ታይላንድ የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ደገፈች

AMN- ነሐሴ 23/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከጂኦግራፊያዊና ከኢኮኖሚያዊ ዕድገት አንጻር ፍትሃዊና መሠረታዊ በመሆኑ፣ ጎረቤት ሀገራት ጉዳዩን በአግባቡ ሊረዱት እንደሚገባ የታይላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሃሳክ ፑዋንግኬትኬው ገለጹ።

ኢትዮጵያ ካላት እጅግ ከፍተኛ ህዝብ ቁጥር እና ፈጣን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አኳያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄን እንደ ህልውና አጀንዳ አድርጋ እየሰራችበት ይገኛል።

የቀጣናው ግዙፍ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ የጂኦግራፊ እስረኛ ሆና መቀጠል እንደማትችል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ የገለጹ ሲሆን፤ ይህንን ጥያቄዋን በንግድና በሰጥቶ መቀበል መርህ ብቻ ለማሳካት በቀጣይነት ጥረት እያደረገች መሆኑ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉት የታይላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሃሳክ ፑዋንግኬትኬው፣ የባሕር ወደቦች ለአንድ ሀገር ንግድና ኢንቨስትመንት እጅግ ወሳኝ ምሰሶዎች መሆናቸውን አመልክተዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ጎረቤት ሀገራት አግባብነት ባለው መልኩ ሊረዱት የሚገባ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ አያይዘውም፣ የባሕር በር የማግኘት ሂደቱ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን የጋራ ጥቅም፣ ሰላምና የዕድገት ትስስር መሠረት ባደረገ መልኩ ሊከናወን እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄም በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት መካከል ሊኖር ከሚገባው ሰፊ የትብብር ማዕቀፍ ጋር በቀጥታ የሚተሳሰር መሆኑን አንስተዋል።

በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረኮች በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ድምፃቸውና ፍላጎታቸው ተሰሚነት እንዲያገኝ በጋራና በትብብር መስራት እንዳለባቸው የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሃሳክ ፑዋንግኬትኬው፤ የደቡብ ንፍቀ ክበብ ሀገራት በዓለም አቀፉ ሥርዓት ውስጥ የጋራ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቀራርበው መስራት እንደሚገባቸው አብራርተዋል።

በዚህ ረገድም አፍሪካ ለዚህ ትብብር ዋነኛ ድምጽ ሆና እየወጣች መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን፣ አፍሪካን ከእስያ አህጉር ጋር በማስተሳሰር ረገድ ወሳኝ የመግቢያ በር ሆና እያገለገለች መሆኑን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ትብብርን እና በሕግ ላይ የተመሠረተውን ዓለም አቀፍ ሥርዓት ለማስጠበቅ ተመሳሳይ አመለካከት ባላቸው ሀገራት መካከል የጠበቀ ወዳጅነትና አንድነት እንዲጠናከር ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review