መንግሥት የዜጎችን ኑሮ ማሻሻልና ዘላቂ ብልጽግናን ማረጋገጥ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጓል – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

You are currently viewing መንግሥት የዜጎችን ኑሮ ማሻሻልና ዘላቂ ብልጽግናን ማረጋገጥ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጓል – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

AMN – ነሐሴ 28/2018 ዓ.ም

መንግሥት ሀገራዊ ሪፎርሞችን በመተግበር የሕዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የገባውን ቃል ወደ ተግባር እየለወጠ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥና የዜጎቿን ሕይወት ከፍ ለማድረግ በምታደርገው ያልተቋረጠ ርብርብ፣ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ የሚያበስሩ ታሪካዊ ምዕራፎች እውን እየሆኑ ይገኛሉ።

መንግሥት ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስልታዊ ፖሊሲዎችን በመንደፍና በመተግበር በኢኮኖሚውና በማኅበራዊው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጦችን በማስመዝገብ ላይ ይገኛል።

በዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ይፋ የተደረገው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) መካከል የተደረሰው ታሪካዊ ስምምነት የዚህ አበይት ርዕይ አንዱ ማሳያ ነው።

በ100 ቢሊዮን ብር ካፒታል የሚቋቋመውና ዓለም አቀፍ አጋርነትን ያካተተው የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ፣ በባንክ ዘርፍ ያለውን የጥሬ ገንዘብ ፍሰት አለመመጣጠን በመቅረፍ ለዜጎች አስተማማኝ የፋይናንስ አቅርቦት ይፈጥራል።

ይህ ታሪካዊ ስምምነት መንግሥት በተመጣጣኝ ዋጋ የኢትዮጵያውያንን ክብር የጠበቁ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶችን ለማቅረብ ያስቀመጠውን ግብ በግንባር ቀደምትነት የሚያሳካ ነው።

ስምምነቱ የዜጎችን የቤት ባለቤትነት ፍላጎት እውን በማድረግ ረገድ የሚታዩ ማነቆዎችን በመስበር፣ የበርካቶችን የዕለት ተዕለት ሕይወትና ማኅበራዊ ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያሻሽል የመንግሥት ቁርጠኝነትን ያረጋገጠ ቁልፍ እርምጃ ነው።

ይህ ስኬት ብቻውን የቆመ አይደለም፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና በሜጋ ፕሮጀክቶች የተመዘገቡት የኢትዮጵያን የማንሰራራት ድሎች ቀጣይ ምዕራፍ አካል ነው።

የመደመር መንግሥት የግል ዘርፉን ተሳትፎ በስፋት በማካተትና የገበያ ሥርዓቱን በማዘመን ሀገራዊ የኢኮኖሚ አቅምን ማጠናከር የልማት ጉዞው መሠረት አድርጎ ቀጥሏል።

እንደ ሀገር እየተመዘገበ ካለው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ጋር ተያይዞ በሚፈጠር የዋጋ ግሽበት አነስተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚደርሰውን ተጋላጭነት ለመቀነስ፣ መንግሥት በቢሊዮኖች የሚቆጠር በጀት በመመደብ በነዳጅ፣ በመሠረታዊ ፍጆታዎች እና በግብርና ግብዓቶች ላይ ከፍተኛ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል።

ከዚህ የዕለት ኑሮ ማቃለያ ሥራ ባሻገር የዜጎችን ኑሮ በዘላቂነት ማሻሻልና ብልጽግናን ማረጋገጥ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጓል።

በዚህም ቃል በተግባር እየተለወጠ ፈጣን፣ ጠንካራ እና ሁሉንም ያካተተ ኢኮኖሚ የመገንባት ጽኑ ፍላጎቱ በሁሉም መስክ በተግባር እየተፈጸመ ቀጥሏል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review