ኤርትራ የኢትዮጵያ ጠላቶች መጠለያ መሆኗን አቁማ ወደ መልካም የጎረቤትነት አቅጣጫ ልትመጣ ይገባል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር)

You are currently viewing ኤርትራ የኢትዮጵያ ጠላቶች መጠለያ መሆኗን አቁማ ወደ መልካም የጎረቤትነት አቅጣጫ ልትመጣ ይገባል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር)

AMN – ጥቅምት 9/2019 ዓ.ም

የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያ ጠላቶች መሣሪያ መሆኑን ትቶ ወደ መልካም የጎረቤትነትና የልማት አጋርነት አቅጣጫ ሊመጣ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢቢሲ ጋር በትግሪኛ ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፤ ኤርትራ ከነፃነት በፊት የነበራት ብልፅግናና የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ ተዳክሟል።

ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል በነበረችበት ጊዜ ከ300 በላይ ፋብሪካዎች የነበሯትና ከአፍሪካ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ከሚባሉት አንዷ እንደነበረች ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ዛሬ ግን ከተሞቿና ነዋሪዎቿ ከነፃነት በኋላ የነበራቸውን ሁሉ ማጣታቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የአሥመራ፣ የምፅዋና የዓሰብ ከተሞች ገጽታ በእጅጉ ተጎሳቆለ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ፤ ታታሪና እንግዳ ተቀባይ የነበረው የኤርትራ ሕዝብም ስደትና ችግር መገለጫው እንዲሆን ተደርጓል ብለዋ።

ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የሻዕቢያ አስተዳደር የሕዝቡን ልማት ወደ ጎን በመተው የኢትዮጵያ ጠላቶች መጠለያና መሣሪያ ለመሆን በመምረጡ እንደሆነ አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ለኤርትራ መንግሥት ከጀርባ ሆነው ድጋፍ የሚሰጡና አይዞህ የሚሉ አካላት የራሳቸውን ችግር እንኳን መፍታት ያልቻሉ በመሆናቸው ለኤርትራ ሕዝብ የሚተርፍ መፍትሔ ሊያመጡ እንደማይችሉ ተናግረዋል።

እነዚህ አካላት ጥይት ከመስጠት ባለፈ የኤርትራን መሠረታዊ ችግሮች የመፍታት ፍላጎትና አቅም የላቸውም ብለዋል።

ባለፉት 35 ዓመታት የታየው እውነት ጥሩ ጎረቤትነትና ወንድማማችነት ብቻ የሚጠቅም መሆኑን እንደሆነ ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ኤርትራ የልማት አጋር ከመሆን ይልቅ የጠላቶች መሸሸጊያ መሆኗን ልትገታ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያን ጥሪ ሰምተው ወደ መልካም አቅጣጫ ካልመጡ ዋጋው እጅግ ከባድ ይሆንባቸዋል ሲሉ አጥብቀው አስገንዝበዋል።

በታደሰ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review