AMN- ነሐሴ 30/2018 ዓ.ም
ሀገሪቱ የጀመረችውን አጋዥ እና ተስፋ ሰጪ የልማት ጉዞ ለማስቀጠል ብሎም የህዝብ ሀብት እንዳይባክን ለመከላከል የሚደረገው የሙስና እና የብልሹ አሰራር ትግል ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የህግ ባለሙያና አማካሪው ግርማ መኮንን(ዶ/ር) ገለጹ።
ግርማ(ዶ/ር) ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ሙስና ዓለም አቀፍ በሽታ መሆኑን ጠቅሰው፡ ሀገራት የራሳቸውን የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት የመከላከል ስልቶችን እንደሚከተሉ አብራርተዋል።
በኢትዮጵያም በቅርቡ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን የጠቆሙት የህግ ባለሙያው፣ የተጀመሩት በጎ ስራዎች የበለጠ ዘላቂነት እና ተከታታይነት ሊኖራቸው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በተጨማሪም ባለሙያው ሙስና ማለት ገንዘብ መቀበል ወይም መስጠት ብቻ እንዳልሆነ ገልጸው፤ አገልግሎት ፈላጊን ማንገላታት፣ ውሳኔ ሳያገኙ ማመላለስ እንዲሁም ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት አለመስጠት ትልቁ የሙስና መገለጫ መሆኑን አስረድተዋል።
መንግስት አሰራሮችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማስደገፍ እና ግልጽነት ያለው አሰራር ለመዘርጋት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ያደነቁት ግርማ(ዶ/ር)፤ በተለይም በቅርቡ የተዘረጉት የዲጂታል እና የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች ብልሹ አሰራርን በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ በመሆናቸው ተስፋፍተው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ሙስና የፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያዛባና የሀገርን ሰላም የሚያናጋ በመሆኑ ችግሩን ከስር መሰረቱ ለማስቀረት ከቤተሰብ እና ከትምህርት ቤት ጀምሮ በትውልዱ ላይ የስነ-ምግባር እና የሀገር ፍቅር ግንዛቤን ማጎልበት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በአስማረ መኮንን