የቱሪዝም ዘርፍ እመርታ ለኢኮኖሚ ዕድገት የማይተካ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

AMN- ጳጉሜን 1/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቱሪዝም ዘርፍ ያስመዘገበችው እመርታ ሀገሪቱን አዲስ ገጽታ እያጎናጸፋት ይገኛል።

መንግሥት ዘርፉን እንደ ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶ በመቅረጽ የወሰዳቸው ቁልፍ የፖሊሲ ማሻሻያዎች እና የልማት እርምጃዎች የሀገሪቱን የኢኮኖሚ አቅጣጫ ከፍ ወዳለ ደረጃ እየወሰዱት ይገኛሉ።

ቱሪዝምን ከተፈጥሮ ጥበቃ እና ከማህበረሰብ ልማት ጋር ያቀናጁት እንደ «ገበታ ለሸገር»፣ «ገበታ ለሀገር» እና «ገበታ ለትውልድ» ያሉ ፕሮጀክቶች እውን መሆናቸው በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን መሳብ አስችሏል።

እነዚህ ውብ መዳረሻዎች ለሀገሪቱ የውጪ ምንዛሬ ገቢ ማደግ እና ለዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች ታላላቅ የሀገሪቱ ከተሞች የተከናወኑ የኮሪደር እና የወንዞች ዳርቻ የልማት ሥራዎች የከተማ ቱሪዝምን በእጅጉ አነቃቅተውታል።

የዘመናዊነት እና የባህል ውህደት ውጤት የሆነው ይህ የእመርታ ጉዞ የከተሞችን ውበት ከማጎልበቱም በላይ የቱሪዝሙን ገጽታ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል።

በሌላ በኩል የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ባሉበት ሆነው በዲጂታል ቴክኖሎጂ የኤሌክትሮኒክ ቪዛ በቀላሉ ማግኘት መቻላቸው የጎብኚዎችን ፍሰት በእጥፍ እንዲያድግ አድርጎታል።

ከውጭ ጎብኚዎች ባለፈም የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ታይቶ የማይታወቅ ዕድገት እያሳየ ይገኛል።

የቱሪዝም ዘርፍ እመርታ የሀገሪቱን አወንታዊ ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ ረገድ የማይተካ ሚና ያለው ሲሆን፣ ይህ ዕድገት በዘላቂነት እንዲቀጥል የቱሪዝም መዳረሻዎችን በዘመናዊ መንገድ የማልማትና አገልግሎቶችን የማዘመን ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review