AMN- ጳጉሜን 02/2018 ዓ.ም

የአዲስ አመት መቀበያ የሆነችውን የጳጉሜን ወር ቀናት በተለያዩ ስያሜዎች እየተከበሩ ይገኛሉ፡፡ የዛሬው ጳጉሜን 2 ደግሞ በማንሰራራት ተሰይሟል።
የአዲስ አበባ የማንሰራራት ማሳያ የሆነው የትራንስፖርት ዘርፍም ለከተማዋ ነዋሪዎች ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ቀኑን እያከበረ ይገኛል።
ለግማሽ ቀን በሚቆየው ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የከተማ አውቶብስና የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ለደንበኞቻቸው መልካም የአዲስ አመት በመመኘት ጭምር እየተሳተፉ ነው።

በቦሌ ሚሊኒየም አካባቢ የተሰጠውን ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት ያስጀመሩት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳኛቸው ሽፈራው በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በነጻ ትራንስፖርቱ 1.1 ሚሊየን የመዲናዋ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።
የአዲስ አበባ የማንሰራራት ማሳያ ከሆኑ ልማቶች መካከልም የትራንስፖርት ዘርፉ ዋነኛው ነው ያሉት አቶ ዳኛቸው፣ የአዲስ አበባን ዝማኔ የሚመጥኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማስፋፋት ዘርፉን ማንሰራራት ተችሏል ብለዋል።
ምቹ መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋትና የዘመነ አገልግሎትም በዘርፉ መሻሻል ማሳየቱን ነው ምክትል ቢሮ ኃላፊው የገለጹት።
በፍቃዱ መለሰ