AMN – ነሐሴ 16/2018 ዓ.ም

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በሀገራዊ ምክክር ማጠቃለያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ በፈተናዎች ጊዜ ሁሉ በውይይትና በማኅበራዊ እሴቶች የመጽናት አቅም እንዳላት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በጥንታዊ ሥልጣኔዋ፣ በማኅበራዊ ትስስሯና በጋራ መስዋዕትነቷ የጸናች ሀገር መሆኗንም ፕሬዝዳንቱ አንስተዋል።
ሀገሪቱ የውስጥ ችግሮቿን በራሷ ማኅበራዊ ጥበብ፣ እውቀትና ትዕግስት የመፍታት አቅም እንዳላት ምክክሩ ማሳያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የሚሰነዘሩባትን “ልትፈርስ ነው” ወይም “መስቀለኛ መንገድ ላይ ነች” የሚሉ ትረካዎችንና የሥጋት ቃላትን በመሻገር፣ የሰላም፣ የትዕግስት እና የመከባበር እሴቶች ባለቤት መሆኑንም አብራርተዋል።

የምክክሩ ሂደት ጊዜያዊ የፖለቲካ መፍትሄ ለማግኘት የተደረገ ሳይሆን፣ ለሀገር ዘላቂ ዕድገት፣ ሰላምና ብልጽግና የሚበጅ ፉኖተ ካርታ መሆኑን ገልጸዋል።
በመድረኩ የተደረገው የሐሳብ ልውውጥ፣ የመደማመጥና የመከባበር ሂደት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አዲስና ተስፋ ሰጪ ምዕራፍ የከፈተ ነው።
በምክክሩ የተገኙ ውጤቶችና ምክረ-ሀሳቦች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለአስፈጻሚና ለሚመለከታቸው አካላት ቀርበው ወደ ተግባር እንደሚለወጡ አመላክተዋል።
ኢትዮጵያዊያን ሁልጊዜም መምከር እንደሚችሉና፣ በመካከላቸው የታየው መደማመጥ እና መከባበር ደግሞ ለነገ ሀገራዊ ተስፋ መሆኑን አሳይቷል ብለዋል።
በመጨረሻም ፕሬዝዳንቱ፤ እየተማከርን ሀገር እንገነባለን፤ ሀገር እየገነባንም እንመካከራለን ይህም ለነገዋ ኢትዮጵያ ትልቅ የተስፋ መሆኑን ገልጸዋል።
በበረከት ጌታቸው