AMN- ጳጉሜን 4/2018 ዓ.ም
ጳጉሜን 4 የኅብር ቀንን አስመልክቶ ሃገር አቀፍ ነፃ ሕክምና እና የምርመራ አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡
ነፃ የሕክምና እና የምርመራ አገልግሎቱ በመስቀል አደባባይ እየተሰጠ ሲሆን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ሰራተኞች እና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተሳተፉበት የአካል ብቃት እንቅስቃሴም ተካሂዷል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ የኅብር ቀንን በጋራ በተለያዩ ፕሮግራሞች ስናከብር ኅብረ ብሄራዊ አንድነታችንን በማስጠበቅ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ለማሸጋገር ሁላችንም በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል።
በመስቀል አደባባይ በተደረገው የነፃ ምርመራ እና ሕክምና አገልግሎት 30 የግል እና 15 የመንግሥት የጤና ተቋማት ተሳትፈዋል።
በመርሃ ግብሩ የአይን፣ የጆሮ፣ የአንጀት፣ የቆዳ፣ የውስጥ ደዌ፣ የቀዶ ሕክምና፣ የማህፀን፣ የካንሰር፣ የላቦራቶሪ እና የዲያግኖስቲክስ ነፃ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል።
የኅብር ቀንን አስመልክቶ በተዘጋጀው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በአዲስ አበባ ብቻ በአንድ ቀን ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች አገልግሎት ይሰጣል፡፡
በሃገር አቀፍ ደረጃ በ12 ክልሎች እና 2 ከተማ አስተዳደሮች ከ200 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ነፃ የምርመራ እና ህክምና አገልግሎት ያኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።