AMN- ጳጉሜን 05/ 2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የዲጂታል ሽግግሯን በብቃት ለመምራት የሚያስችላትን ግልጽ ስትራቴጂ ነድፋ ወደ ተግባር መግባቷን የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ገልጸዋል።
ይህንኑ ስትራቴጂ ስኬታማ ለማድረግ የሰው ሃይል ልማት፣ ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችና የሳይበር ደህንነት በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
“ነገን ዛሬ መገንባት፣ ዲጂታል ሽግግር፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ የምግብ ሉዓላዊነትና ሀገራዊ የአደጋ ስጋት አስተዳደር ለኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ሃሳብ “የነገ ቀን”በሳይንስ ሙዚየም በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።

አፈ ጉባኤው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ፣ ቴክኖሎጂ በሀገራችን እያደገ የመጣውን “የምክክር ባሕል” ይበልጥ በማስፋት ሁሉም ዜጋ በንቃት እንዲሳተፍና ሀሳቡ እንዲደመጥ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ጠቁመው፤ በተለይም ወጣቶች የዕለቱን “የነገ ቀን” እሳቤ በመላበስ “ነገን አትጠብቁ፤ ነገን ዛሬ ስሩ!” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤትም ይህንን ሀገራዊ የዲጂታል ሽግግር የሚደግፉ የሕግ ማዕቀፎችን በማውጣት የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) በበኩላቸው አንድ የዲጂታል አገልግሎት የበርካታ ተቋማትን ቅንጅትና መረጃ የሚጠይቅ በመሆኑ ጠንካራ የጋራ አሠራር ሥርዓትን መገንባት የግድ ይላል ብለዋል።
ሚኒስትሩ የዲጂታል ኢትዮጵያን ሽግግር እና የነገዋን የበለጸገች ሀገር ራዕይ በአስተማማኝ ሁኔታ እውን ለማድረግ የሳይበር ደህንነት ጉዳይ የስትራቴጂው ዋና ምሰሶ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዛሬ የምንገነባው ዲጂታል መሠረተ-ልማት ለነገው ትውልድ ደህንነቱ የተረጋገጠ እና ከጥቃት የተጠበቀ መሆን ይኖርበታል መለታቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር መረጃ ያመላክታል።