AMN- መስከረም 3/2019 ዓ.ም
የብሪክስ “ኒው ዴቭሎፕመንት” ባንክ በማደግ ላይ ያሉ ሃገራት ቅድሚያ በሚሰጧቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተቋማትን መገንባት እንዲችሉ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የብሪክስ አባል እና ወዳጅ ሀገራት ትብብር ትርጉም ያለው ሚና ሊኖረው ይገባል ብለዋል፡፡
አንድነት ጠንካራ የሚሆነው እያንዳንዱ አባል ሀገር ድምፅ መደመጥ ሲችል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ መርህ እስከ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሊዘልቅ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በተባበሩት መንሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ ውክልና እንዲኖራት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት በኩል የቀረበውን የጋራ አቋም እንደምትጋራ ተናግረዋል።
በብሪክስ ውስጥ ለአፍሪካ ውክልና የሚደረገው ድጋፍ ወደ ተግባር መቀየር እንዳለበትም አንስተዋል፡፡
“ኒው ዴቭሎፕመንት” ባንክ በማደግ ላይ ያሉ አገራት በራሳቸው ቅድሚያ በሚሰጧቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተቋማትን መገንባት እንደሚችሉ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት ከምንም በላይ ለኢኮኖሚያዊ ግስጋሴዋ ወሳኝ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እንደ ትልቅ እና በማደግ ላይ ያለ ኢኮኖሚ አስተማማኝ እና ባለብዙ አማራጭ ዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች ማግኘት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሰላማዊ እና በድርድር በሚደረሱ ስምምነቶች ይህንን ግቧል ለማሳካት እንደምትቀጥልም አመላክተዋል፡፡
በወርቅነህ አቢዮ