AMN – መስከረም 5/2019 ዓ.ም

የኤሌክትሪክ ትራንስፖርት የኢንቨስትመንት ዕድሎች እንዲስፋፉ የተሟላ ሥነ-ምህዳር መፍጠር እንደሚገባ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን አገልግሎት ከማስፋፋት ባለፈ በኃይል መሙያ መሠረተ ልማት፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በጥገና እንዲሁም በክህሎት ልማት ላይ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት በሳይንስ ሙዚየም በተካሄደው የኖርዲክ–አፍሪካ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው።
ወደ ኤሌክትሪክ ትራንስፖርት የሚደረገው ሽግግር ተሽከርካሪዎችን ከማብዛት ባሻገር፤ የኃይል መሙያ መሠረተ ልማትን፣ የዲጂታል ሥርዓትን፣ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን፣ የጥገና ማዕከላትን እና የሰው ኃይል ክህሎትን ያካተተ የተሟላ ሥነ-ምህዳር መፍጠር እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።
ይህን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የመንግሥት ሀብት ብቻውን በቂ ስለማይሆን ከልማት አጋሮች፣ ከባንኮች፣ ከባለሀብቶች እና ከኢንዱስትሪ ባለቤቶች ጋር አጋርነት መፍጠር እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

በተጨማሪም የሽግግሩ ሂደት ሴቶችን፣ ወጣቶችን እና አካል ጉዳተኞችን ያካተተና ተጠቃሚ የሚያደርግ ሊሆን እንደሚገባው አፅንኦት ሰጥተዋል።
ትኩረቱም በኤሌክትሪክ በሚሰሩ የብዙኃን የትራንስፖርት አማራጮች እና በተቀናጀ የትራንስፖርት ሥርዓት ላይ መሆን እንዳለበት አንስተዋል።
ዘላቂ እና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ትራንስፖርት ለመገንባትም ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከጥናት ማዕከላት እና ከኢንዱስትሪዎች ጋር በመቀናጀት ብቁ መሐንዲሶችን፣ ቴክኒሻኖችን፣ ተመራማሪዎችን እና የፖሊሲ ባለሙያዎችን ማፍራት ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ (ዶ/ር) አለሙ ማሳሰባቸውን ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።