በቀጣናው ያሉ ፈተናዎችን በዘላቂነት ለመፍታት የሀገራት የጋራ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው – ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)

AMN – መስከረም 5/2019 ዓ.ም

በቀጣናው የሚያጋጥሙ ፈተናዎች በዘላቂነት እንዲፈቱ የአባል ሀገራት አብሮነትና የጋራ ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት 74ኛው አስቸኳይ ስብሰባውን ዛሬ በጅቡቲ አካሂዷል።

በስብሰባው ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የኢጋድ አባል ሀገራት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

በቀጣናው ሰላም እና ጸጥታ እንዲሁም በሌሎች አበይት ጉዳዮች ላይ ምክክር ተደርጓል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በቀጣናው እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን በዘላቂነት ለመቋቋም የአባል ሀገራት አብሮነትና የጋራ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው።

በኢጋድ ሴክሬታሪያት በኩል የተከናወኑ የልማትና የሰላም ሥራዎች አበረታች ውጤቶችን እያስገኙ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ተቋሙ ለቀጣናው ህዝቦች ብልጽግና መረጋገጥ የጸና አቋም እንዳለው አመልክተዋል።

ምንም እንኳን የተለያዩ ጂኦፖለቲካዊ ፈተናዎች ቢኖሩም፣ የኢጋድ ሴክሬታሪያት ያለፉት ስድስት ወራት አፈጻጸም አበረታች የሚባል መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣናዊ መሠረተ ልማት እና የጤና ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን ያነሱት ዋና ፀሐፊው፤ የቀጣናው የከርሰ ምድር ውሃ መረጃ ሥርዓት የአገልግሎት ተደራሽነት የላቀ ውጤት ማስመዝገቡን ጠቁመዋል።

እንዲሁም የቀጣናው ዓለም አቀፍ የጤና ሽፋን መረጃ ጠቋሚ (ኢንዴክስ) ከ60 ወደ 65 በመቶ ከፍ ማለቱንና ይህም እ.አ.አ በ2027 70 በመቶ ለማድረስ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የሚያስችል መሆኑን ነው ያነሱት።

በሌላ በኩል ሱዳን ወደ ኢጋድ ሙሉ አባልነቷ መመለሷ የቀጣናውን ትብብርና አንድነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።

ዋና ፀሐፊው እ.አ.አ ጁላይ 2026 ወደ ሱዳን ባቀኑበት ወቅት የኢጋድ የሱዳን ልዑክ ቢሮ በድጋሚ በይፋ መከፈቱን አስታውሰው ይህ እርምጃ ከቀጣናው ሕዝቦች ጋር ያለውን ቀጥተኛና ዘላቂ ትስስር አጠናክሮ የሚያስቀጥል መሆኑን አመላክተዋል።

ኢጋድ ከአፍሪካ ሕብረት፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች እና ከሌሎች ስትራቴጂካዊ አጋሮች ጋር ያለው ግንኙነት ለቀጣናው ዘላቂ ልማት ወሳኝ ነው ብለዋል።

አጋርነቱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን አቅም በማጠናከር ረገድ የጎላ ድርሻ እንደሚያበረክትም ነው ያነሱት።

በቀጣይ ሊከሰቱ የሚችሉ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎችን የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን በማጠናከር ለመቋቋም የሚያስችሉ አሰራሮች እየተቀረፁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሀገራት የኤልኒኖ የአየር ንብረት መዛባት የሚያስከትለውን ስጋት ለመቀነስ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በሌላ በኩል ቀጣናውን ከሰው ሰራሽ አስተውሎት ጋር ለማስተሳሰርና በቴክኖሎጂ የታገዘ የልማት መሠረት ለመጣል የተጀመሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ስብሰባው የቀጣናውን ሰላም፣ ደህንነት እና ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማፋጠን በሚያስችሉ ሀገራዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በመምከርና ውሳኔዎችን በማሳለፍ መጠናቀቁን ከኢጋድ ሴክሬተሪያት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review