AMN- መስከረም 9/2019 ዓ.ም
በርካታ የዓለም ሃገራት የከተማቸዉንና የአካባቢያቸዉን ጽዳት ለማረጋገጥ ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ዉብና ጽዱ ከተማ ከመፍጠር አልፈዉ ለተቀረዉ ዓለም ምሳሌ እስከመሆን ደርሰዋል፡፡
ጃፓን በንጽህናዋ እና በቆሻሻ አያያዝ ሥርዓቷ ቀዳሚዋ ስትሆን፤ ዜጎቿ ቆሻሻዎችን ከቤታቸው ጀምሮ ሲያስወግዱ ፕላስቲክ፣ ወረቀት፣ ተፈጥሯዊ እና ብርጭቆ መሰል ቆሻሻዎችን በከፍተኛ ጥንቃቄ ለይተዉ የማስወገድ ልምድ አላቸዉ፡፡
የጃፓን ትምህርት ቤቶችም ተማሪዎች የራሳቸውን ክፍል እና ትምህርት ቤት በራሳቸው አቅም እንዲያጸዱ የምታደርግ ሲሆን፣ ይህም ዜጎቿ ከህጻንነት ጀምሮ በቆሻሻ አወጋገድ ላይ ሃላፊነት እንዲወስዱ የሚያደርግ ነዉ፡፡
ሲንጋፖር በተመሳሳይ መልኩ የከተማዋን ጽዳትና ውበት ለማስጠበቅ እጅግ ጥብቅ ህጎች ያሏት ሲሆን፣ በየቦታዉ ቆሻሻ መጣል እና ማስቲካ አኝኮ መትፋት ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት ያስቀጣል።
የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቷም እጅግ በጣም የዘመነ ሲሆን፣ የሃገሪቱ መንግስትና ዜጎቿ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከተማቸዉን ሁልጊዜ ንጹህ አድርገዉ ለማቆየት በጋራ ይሰራሉ፡፡
ስዊዘርላንድ እና ዴንማርክም ጽዱ መዲና በመፍጠር ረገድ የተሻለ ተሞክሮ ያላቸዉ ሃገራት ናቸዉ፡፡ ሃገራቱ ከፍተኛ መጠን ያለውን ቆሻሻ የጽዳት ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመዉ ከማስወገዳቸዉም በላይ ቆሻሻዎችን አቃጥለዉ ለአካባቢ ንጹህ የሆነ ኤሌክትሪክ እና የሙቀት ኃይል ያመነጫሉ፤ እንዲሁም የብስክሌት ባህል በመስፋፋቱ የከተማቸዉ አየር ከብክለት የጸዳ ነው።
የእነዚህ ሃገራት ስኬት የተመሰረተው በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በእያንዳንዱ ዜጋ የባህሪ ለውጥ እና ኃላፊነት ስሜት ላይ ነው።
መዲናችን አዲስ አበባም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት በመከተል፤ ቆሻሻን መልሶ በመጠቀምና የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ለአፍሪካና ለተቀሩት ከተሞች ምሳሌ ሆናለች፡፡
አዲስ አበባ ላይ ዛሬ በዘፈቀደ ቆሻሻ በየቦታዉ አይጣልም፤ ቆሻሻን የሚጸየፍ ማህበረሰብ ተፈጥሯል፤ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎችን ለይቶ የማስወገድ ባህልም ተሻሽሏል፤ ህገወጥ በሆነ መንገድ ቆሻሻን ማስወገድም ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን ነዋሪዎች በማስተባበር ባከናወናቸዉ የኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች መዲናዋ አዲስ ገጽታን ከመላበሷም በላይ ጽዱ፤ አረንጓዴና ዉብ አበባ ሆናለች፡፡
በዘርፉ በሰራዉ ስራ የከተማ አስተዳደሩ እዉቅና እስከማግኘት የደረሰ ሲሆን በርካታ የአፍሪካ ሃገራትም ይህንኑ ተሞክሮ በመቀመር ላይ ይገኛሉ፡፡
በየአመቱ የሚካሄደዉ ዓለም አቀፍ የፅዳት ቀንም እነዚህን ተሞክሮዎች በማስፋት ረገድ ትልቅ እድል የሚፈጥር ሲሆን ዓላማውም በምድር ላይ ያለውን የፕላስቲክ እና የቆሻሻ መበከል አደጋ ለመቀነስ እንዲሁም ማህበረሰቡን ስለ አካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው።
በዚህ ንቅናቄ ላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ድርጅቶች የሚሳተፉ ሲሆን ቆሻሻዎችን በማንሳት፣ ሕገ-ወጥ የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎችን በማጽዳት እና ዘላቂ የቆሻሻ አያያዝ ልምዶችን በማስፋፋት ዕለቱን ያከብራሉ፡፡
ንቅናቄዉ የውሃ አካላትን፣ መሬትን እና ከተሞችን ከፕላስቲክ እና አደገኛ ቆሻሻዎች በመጠበቅ የብዝሃ-ሕይወት ቀውስን ለመከላከል ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
በወንድማገኝ አሰፋ