AMN – መስከረም 27/2019 ዓ.ም

የ18 ቁጥር ማዞሪያ የቀለበት መንገድ እየተከናወነ ባለው የመንገድ ግንባታ ምክንያት ከቅዳሜ መስከረም 30 ጀምሮ በጊዜያዊነት ለትራፊክ እንቅስቃሴ ዝግ እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡
በግንባታ ላይ ያለው ከመርካቶ – በመሣለሚያ ወደ 18 ቁጥር ማዞሪያ የሚወስደው የመንገድ ፕሮጀክት 18 ቁጥር ማዞሪያ አካባቢ የላይ እና የታች የትራፊክ ማሳለጫ ድልድይ የሚያካትት መሆኑን የጠቀሰው ባለሥልጣኑ ፣ ለግንባታው መፋጠን ሲባል የ18 ቁጥር ማዞሪያ የቀለበት መንገድ በጊዜያዊነት ዝግ እንደሚደረግ ጠቅሷል፡፡
በመሆኑም ከቅዳሜ መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ አሽከርካሪዎች ሌሎች የመንገድ አማራጮችን እንዲጠቀሙ ባለሥልጣኑ አሳስቧል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን እንደየተሸከርካሪዎቹ አይነቶች የጠቆማቸው አማራጭ የጉዞ መሥመሮች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
1ኛ. ከአየር ጤና፣ ከ3 ቁጥር ማዞሪያ ወይም ከጦር ኃይሎች አቅጣጫ ወደ ዊንጌት፣ ሸጎሌና አዲሱ ገበያ የሚጓዙ የከባድ መኪና ተሽከርካሪዎች፤
አማራጭ 1፦ ከጦር ኃይሎች
ኮካ/ልደታ አደባባዮች
አማኑኤል/አብነት
አጣና ተራ
ዊንጌት / ሸጎሌ / አዲሱ ገበያ፤
አማራጭ 2፦ ከጦር ኃይሎች
በኔዘርላንድ (ሆላንድ) ኤምባሲ አካባቢ ባለው የትራፊክ መብራት በኩል ወደ ቀኝ በመታጠፍ፣ ከአባ ጂፋር መስጂድ / በገዳም ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን አቅጣጫ ወደ አማኑኤል ቤተክርስቲያን
መሳለሚያ
አጠና ተራ
ዊንጌት/ ሸጎሌ / አዲሱ ገበያ፤
2ኛ. ከአዲሱ ገበያ / ሸጎሌ ወደ 18 ማዞሪያና ጦር ኃይሎች አቅጣጫ የሚጓዙ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች፤
ኢ.ቢ.ሲ አዲሱ ጣቢያ አካባቢ ሲደርሱ፣ ከቀለበት መንገድ በመውጣት ወደ ዊንጌት አደባባይ እንዲያመሩና ከዊንጌት አደባባይ ወደ መድኃኒዓለም መንገድ በመቀጠል፣ ወይም ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ጋር ወደ ቀኝ በመታጠፍ፣ በጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ጀርባ በኩል አድርገው ወደ ታይዋን ገበያ ከዚያም ወደ መሳለሚያ እንዲጓዙ ይመከራል።
ስለሆነም ከአዲሱ ገበያ ወይም ከሸጎሌ አቅጣጫ ወደ 18 ማዞሪያ ወይም ጦር ኃይሎች የሚጓዙ ከባድ ተሽከርካሪዎች፣ ዊንጌት አደባባይ ላይ ባለዉ የላይኛውን መተላለፊያ ድልድይ መጠቀም የማይፈቀድ መሆኑን ያሳውቃል።
3ኛ. የቀላል እና መካከለኛ ተሽከርካሪ አሽከርካሪዎች፦
ከአየር ጤና፣ ከ3 ቁጥር ማዞሪያ ወይም ከጦር ኃይሎች አቅጣጫ ወደ ዊንጌት፣ ሸጎሌና አዲሱ ገበያ ለመጓዝ፦
• ከጦር ኃይሎች አቅጣጫ ከፍ ብሎ ባለዉ ሆላንድ ኤምባሲ አካባቢ ካለው የትራፊክ መብራት ወይም ከአባ ጂፋር መስጂድ ቀጥሎ ባለው የእግረኛ ድልድይ አካባቢ ባለዉ አስፋልት መንገድ ወደ ቀኝ በመታጠፍ፣ ወደ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ጀርባ በሚወስደው አስፋልት መንገድ
መሳለሚያ
አጠና ተራ
ዊንጌት /ሸጎሌ /አዲሱ ገበያ የሚወስደውን መንገድ እንዲጠቀሙ፤
• በተጨማሪም፣ ሌሎች ትናንሽ መኪኖችን የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎች በዚሁ አካባቢ የሚገኙትን የውስጥ ለውስጥ አማራጭ መንገዶች በመጠቀም፣ የትራፊክ ምልክቶችንና የትራፊክ አስተባባሪዎችን መመሪያ በመከተል ወደ ዊንጌት እና አጠና ተራ አቅጣጫ መጓዝ የሚችሉ መሆኑን፤
ከአዲሱ ገበያ / ሸጎሌ ወደ 18 ማዞሪያና ጦር ኃይሎች አቅጣጫ ለሚጓዙ ለቀላል እና መካከለኛ መኪና አሽከርካሪዎች፡
• የዊንጌት አደባባይ ላይኛውን መተላለፊያ ድልድይ በመጠቀም ወደ አጠና ተራ አቅጣጫ መጓዝ የሚችሉ መሆኑን፣
• ሆኖም አጠና ተራ የትራፊክ መብራት ወይም እፎይታ የገበያ ማዕከል አካባቢ ሲደርሱ፣ ከዊንጌት/ሸጎሌ/አዲሱ ገበያ በኩል በውጨኛው የቀለበት መንገድ መስመር (በተለምዶ “50” ተብሎ በሚጠራው) የመንገድ ክፍል የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች፣ የእግረኛ ድልድዩን ከማለፋቸው በፊት ወደ ቀኝ በመታጠፍ፣ ወደ ሚሊኒየም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት
በሙሉ መንገድ በኩል
ልኳንዳ-18 መንገድን በማቋረጥ
ወደ 18 መብራት ኃይል መግቢያ ቀለበት መንገድ በማድረግ
ጦር ኃይሎች መጓዝ ይችላሉ።
• በተጨማሪም ከዊንጌት/ሸጎሌ/አዲሱ ገበያ በኩል በውስጠኛው የቀለበት መንገድ ሌይን (በተለምዶ “80” ተብሎ በሚጠራው) የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች፣ በአጠና ተራ የትራፊክ መብራት ወደ ቀኝ በመታጠፍ ወደ ኮልፌ ፓርክ
በሙሉ መንገድ በኩል
ወደ ልኳንዳ-18 መንገድ
ወደ 18 መብራት ኃይል መግቢያ ቀለበት መንገድ በማድረግ
ወደ ጦር ኃይሎች መጓዝ ይችላሉ።
3. ከልኳንዳና አሸዋ ሜዳ ወይም ወደ ልኳንዳና አሸዋ ሜዳ ጋር ተያያዥ ለሆኑ የትራፊክ ፍሰቶች ያሉ አማራጮችን በተመለከተ፡
3.1 ከአሸዋ ሜዳ/ቡራዩ በ18 ማዞሪያ በኩል ወደ ዊንጌት የሚጓዙ ከባድ ተሽከርካሪዎች በተመለከተ፡-
ከተጠቀሰዉ አቅጣጫ በ18 ማዞሪያ በኩል ወደ ዊንጌት የሚጓዙ ከባድ ተሽከርካሪዎች፣ ከተጨማሪ የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነሰ ሲባል ሌሎች አማራጭ መስመሮች ቀድመዉ እንዲጠቀሙ ይመከራል፡፡
ለዚህም ከአሸዋ ሜዳ /ቡራዩ ወድ አንፎ አደባባይ በአለም ባንክ በኩል ወይም በቀራኒዮ አደባባይ በኩል ወደ ጦር ኃይሎች አቅጣጫ በመጓዝ የጉዞ መስመራቸዉን ቢያስተካክሉ ተመራጭ ነዉ።
3.2 ሆኖም ግን ከልኳንዳ አካባቢ ወደ ጦር ኃይሎች ወይም ወደ ዊንጌት የሚጓዙ ቀላልና መካከለኛ ተሽከርካሪዎች፡-
እነዚህ ቀላልና መካከለኛ ተሽከርካሪዎች 18 ማዞሪያ ቀለበት መንገድ ከመድረሳቸዉ በፊት ባሉ ወደ ግራ እና ወደ ቀኝ በሚታጠፉ ሌሎች አማራጭ መስመሮች እንዲጠቀሙ ይመከራል፡፡
3.3 በተጨማሪም ከዊንጌት /አጠና ተራ ወይም ከጦር ኃይሎች አቅጣጫዎች ወደ ልኳንዳ አካባቢ የሚጓዙ ቀላልና መካከለኛ ተሽከርካሪዎች የሚከተሉት አማራጭ መስመሮች እንዲጠቀሙ ይመከራል፡-
አቅጣጫ – 1 ከዊንጌት /አጠና ተራ አቅጣጫ ወደ ልኳንዳ ለሚጓዙ ቀላልና መካከለኛ ተሽከርካሪዎች፡- ከአጠና ተራ የትራፊክ መብራት ወደ ቀኝ በመታጠፍ ወደ ኮልፌ ፓርክ ከዚያም በሙሉ መንገድ በኩል ወደ ልኳንዳ-18 መንገድ ወደ ልኳንዳ መጓዝ ይችላሉ።
አቅጣጫ – 2 ከጦር ኃይሎች አካባቢ ወደ ልኳንዳ የሚጓዙ ቀላልና መካከለኛ ተሽከርካሪዎች ከአባ ጂፋር መስጂድ ቀጥሎ ባለው የእግረኛ ድልድይ አካባቢ ወደ ግራ በመታጠፍ በ18 መብራት ኃይል መግቢያ ቀለበት መንገድ በማድረግ ወደ ልኳንዳ-18 መንገድ በማድረግ ወደ ልኳንዳ መጓዝ ይችላሉ።
በተጨማሪም ለቀላል ተሽከርካሪዎች በአካባቢዉ ባሉ ሌሎች የውስጥ ለውስጥ አማራጭ መንገዶች በመጠቀም ወደ መድረሻቸው መጓዝ ይችላሉ።
ባለሥልጣኑ ከላይ በተዘረዘሩት ወይም በተዘጋጁት አማራጭ የትራፊክ መስመሮች ላይ የትራፊክ ፍሰቱን ሊያውክ የሚችል ማንኛውም ዓይነት ተሽከርካሪ ለአጭርም ሆነ በቋሚነት ማቆም በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን አሳስቧል።