AMN – መስከረም 11/2019

በርካታ የአለም ሃገራት ለቱሪዝም ኢንዱስትሪዉ በሰጡት ልዩ ትኩረት ዘርፉ ዋንኛ የኢኮኖሚያቸዉ አንቀሳቃሽ ከመሆን አልፎ ከነዳጅና ከኬሚካሎች ቀጥሎ ትልቁ የወጪ ንግድ ለመሆን በቅቷል፡፡
የቱሪዝም ዘርፍ የነፍስ ወከፍ ገቢን ከመጨመር፤ የቴክኖሎጂ እድገትን ከማረጋገጥ፤ መሰረተ ልማቶችን ከማዘመን፤ የስራ እድል ከመፈጠርና አጠቃላይ ሃገራዊ ምርትን ከማሳደግ ረገድ ያለዉ ሚና የጎላ ነዉ፡፡
ኢትዮጵያ በታሪክ፤በባህልና በተፈጥሮ ሀብቶች የታደለች፤ ዘመን የማይሽረዉ ሕብረ ቀለም፤ ኪነጥበብና ሁሉም አይነት የቱሪዝም ሃብቶች ቢኖራትም ለረጂም አመታት ከዘርፉ በሚገባት ልክ አልተጠቀመችም፡፡
ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን መንግስት ለቱሪዝም ልማት በተሰጠዉ ልዩ ትኩረት የቱሪዝም መሰረተ ልማቶችን ከማስፋፋት ጀምሮ ዘርፉን በተለያዩ ማዕቀፎች በመደገፍ የቱሪዝም ኢንዱስትሪዉ እንዲሳለጥ አድርጓል፡፡
ከአዲስ አበባ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ገበታ ለሃገርና ገበታ ለትዉልድ በሚሉ ተነሳሽነቶች የተጀመረዉ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን የማልማት ስራ በሁሉም የሃገሪቱን ማዕዘናት ተዳርሷል፡፡
ከአዲስ አበባ የተጀመረዉ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማትም ቢሆን የኢትዮጵያን ከተሞች ገጽታ በእጅጉ ከመቀየሩም በላይ የተገነቡት የቱሪስት መስህቦች የጎንኚዎችን ምቾት ለመጠበቅና ርካታቸዉን ለመጨመርም አግዟል፡፡
ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪስት መስህቦች ከማስተዋወቅ ጎን ለጎን የግል አስጎብኚ ድርጅቶች ቱሪስቶችን በአግባቡ እንዲያስተናግዱ፤ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶችም አገልግሎታቸዉን እንዲያዘምኑ በርካታ ስራዎች ተከናዉነዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመላዉ አለም እና በሃገር ዉስጥ ካለዉ በርካታ የበረራ መስመሮችና የማጓጓዝ አቅም በተጨማሪ፤ ቱሪስቶች በሚሄዱባቸዉ አካባቢዎች ሁሉ ተገቢዉን መስተንግዶ እንዲያገኙ፤ ምቾትና ደህንነት እንዲሰማቸዉ ለማድረግ በተሰሩ ስራዎች ኢትዮጵያ ቱሪስቶች የሚሸጋገሩባት ብቻ ሳትሆን የሚቆዩባት ለመሆን በቅታለች፡፡
ዘመናዊ የኮንፈረንስ ማዕከላት፣ የኤግዚቢሽን አዳራሾችና የስብሰባ ተቋማት በመገንባታቸው የዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የማስተናገድ አቅሟን አሳድጋለች፡፡
ዘርፉ ለሆቴሎች፣ ለትራንስፖርት ዘርፍ፣ ለንግድ ተቋማትና ለአገልግሎት ሰጪዎች ከፍተኛ የኢኮኖሚ መነቃቃትን ፈጥሯል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ማዕከል ለመሆን ያላትን እድል በመጠቀም በኮንፈረንስ ቱሪዝም ትልቅ ስኬትን ያስመዘገበች ሲሆን ዘርፍ ትልቅ ስኬት አዲስ አበባ ባለፈዉ አመት ብቻ ያላትን ዓለም አቀፍ ተመራጭነት በማጠናከር ከ 200 በላይ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችንና ጉባኤዎችን በስኬት ለማስተናገድ ችላለች፡፡
ቱሪዝም አሁን ላይ የመዝናኛ ብቻ ሳይሆን የሥራ እድል ፈጠራ፣ የገጽታ ግንባታና የባህል ዲፕሎማሲ ሀይል ከመሆኑ አልፎ ከዘርፉ የሚገኘዉ የውጭ ምንዛሪ ገቢም የሃገሪቱን ኢኮኖሚው በመደገፍ ላይ ይገኛል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ