የምግብ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች ታላቅ ሀገር- ኢትዮጵያ

AMN- መስከረም 11/2019 ዓ.ም

ታሪካዊ ጠላቶቿን በመመከት ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ የኖረችው ኢትዮጵያ፤ ያንን የጸና የአንድነትና የድል ታሪክ በኢኮኖሚው ዘርፍ እየደገመች ትገኛለች።

መንግሥት ባከናወነው ሀገር-በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ አማካይነት የሀገሪቱ ሁለገብ አቅም በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቷል።

ከዘመናዊ ሪፎርሞች መካከል “በምግብ ራስን መቻል የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው” በሚል መርህ በግብርናው ዘርፍ የተከናወኑት ስራዎች ሀገሪቱን ከዘመናት የምግብ እርዳታና ከውጭ ስንዴ ጥገኝነት ያላቀቀ ታሪካዊ ምዕራፍ ከፍተዋል።

ቀደም ሲል በሀገር ውስጥ የሚመረተው ስንዴ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ በቂ ባለመሆኑ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በመመደብ ከውጭ ሀገር ይገባ ነበር። ሆኖም አሁን ላይ እየተወሰዱ ያሉ የፖሊሲና የስትራቴጂ እርምጃዎች የሀገሪቱን ገጽታ በዘላቂነት ቀይረውታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “በምግብ ራስን መቻል ዋነኛ አጀንዳችን ነው፤ በምግብ ራስን ለመቻል መሬት፣ ውኃ እና ሰው ያስፈልጋል፤ እነዚህ ደግሞ አሉን” በማለት የወሰዱት ቁርጠኛ አቋም ታላቅ ሀገር ኢትዮጵያን በተግባር ማረጋገጥ ችሏል።

ለዚህ ታላቅ ለውጥ ደግሞ ትልቁ ማሳያ በበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት የተመዘገበው አስደናቂ እመርታ ነው። በሀገሪቱ የተካሄደው የተቀናጀ አሰራርና ሰፊ የሰብል ማልማት እንቅስቃሴ የምርት መጠኑን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።

በ2011 ዓ.ም በ3 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ ብቻ ተሞክሮ የነበረው የመስኖ ስንዴ ልማት አሁን ላይ ከ3.7 ሚሊየን ሄክታር በላይ በመሸፈን ዓመታዊ የስንዴ ምርትን ከ330 ሚሊየን ኩንታል በላይ ማድረሱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

ከዚህ ታሪካዊ ስኬት ጀርባ የኢትዮጵያ የግብርና ሽግግር ዘመናዊ ቴክኖሎጂን እና የሰው ሰራሽ አስተውሎትን (AI) በስፋት እየተጠቀመ መምጣቱ ትልቅ ድርሻ አለው።

ይህም ዘርፉን ምርታማ፣ በገበያ ላይ የተመሰረተ እንዲሁም ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቀውሶችን የመቋቋም አቅሙ የዳበረ እንዲሆን አድርጎታል።

ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር ባደረገው የ2.5 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት በጎዴ ከተማ እየተገነባ ያለው የጉባ ብስራት የሆነው ግዙፍ የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ ሲጠናቀቅ በዓመት 3 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ የማምረት አቅም ይኖረዋል።

ይህም የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረትን በዘላቂነት በመፍታት ለስንዴ ልማቱና ለጠቅላላው የግብርና እድገት ዋነኛ ድጋፍ በመሆን ስኬቱን ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው።

በመደመር እሳቤ እየተመዘገቡ ያሉት እነዚህ ተጨባጭ የግብርና ውጤቶች የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ እያፋጠኑ ሲሆን ኢትዮጵያ በእርግጥም የምግብ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች ታላቅ ሀገር መሆኗን በተግባር ያመላክታሉ።

በትዝታ መንግስቱ

See less

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review