AMN – መስከረም 13/2019 ዓ.ም
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ (AMN) በአዲስ ማዕድ ፕሮግራሙ ”የፀናች ሀገር ወደ መንግሥት ምስረታ እየሄደች ነው” በሚል መሪ ሀሳብ ከተለያዩ ምሁራን ጋር ሰፊ ውይይት አካሂዷል።
በዚህ መድረክ ላይ ተሳታፊ በመሆን ሐሳባቸውን ያካፈሉት የማህበራዊ ልማት አጥኚው አቶ ለሚ ስሜ፣ ሰሞኑን በተለያዩ ኃይሎች የተመሰረተውን አዲስ የኢትዮጵያ ኃይሎች ጥምረት በተመለከተ ጥልቅና አንኳር ትንታኔ ሰጥተዋል።
አቶ ለሚ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ያስፈልጋል ከሚሉ እና አያስፈልግም ከሚሉ ተቃራኒ አካላት ጋር የተደረገው የጋራ ግንባር ምስረታ ጥረት ከጅምሩ መሠረት የሌለውና የቆመበት እውነት የሌለ ስብስብ ነው።
ባለፉት አምስት ዓመታት እንደ ሕዳሴ ግድብ ማጠናቀቅ እና ሀገራዊ ምርጫ ባሉ የሀገሪቱ ድሎች ላይ ጥላ ለማጥላት በርካታ መዋቅራዊና ፖለቲካዊ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።
አጥኚው አሁን ባለው ወቅት እነዚህ የተለያየ ሂደት ያላቸው ቡድኖች ድንገት አንድ ላይ የተሰለፉባቸውን ዋና ዋና ምክንያቶች ሲያብራሩ፦ ቀደም ሲል በተናጠል ያደረጓቸው የትግል ሙከራዎች ሙሉ በሙሉ በመክሸፋቸው የተስፋ መቁረጥ ስሜት በመፈጠሩ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ሌላው አዲስ መንግሥት ከመመሥረቱ በፊት እና መንግሥት ከጊዜ ወደ ጊዜ ጠንካራ እየሆነ ሲመጣ ሊፈጠሩ የሚችሉ ፖለቲካዊ ዕድሎችን ለመቀማት ሲሉ ያደረጉት ጥምረት እንደሆነም ነው ያነሱት፡፡
በተጨማሪም የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማደናቀፍ ከሚሠሩ የውጭ እና የውስጥ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ጋር አብሮ በመሰለፍ የተፈጠረ የውስጥና የውጭ ምቀኝነት ጥምረት መሆኑንም አስረድተዋል።
በህብረቱ ውስጥ የተካተቱት አካላት የራሳቸው የተለያየ እና እርስ በእርስ የሚጋጩ የፖለቲካ ሕልሞች ያሏቸው ከመሆኑም በላይ፣ አንዳንዶቹ ያለፍላጎታቸው ወይም የሌሎች ኃይሎች መጠቀሚያ በመሆን ወደዚህ ጥረት እንደገቡም አቶ ለሚ አብራርተዋል።
በዚህም የተነሳ፣ እንደ ኦብነግ ያሉ ድርጅቶች ስማቸው ያለአግባብና ከፍላጎታቸው ውጭ መጠቀሱን በመግለጽ ከውህደቱ መውጣታቸውን አቶ ለሚ ጠቅሰዋል፤ ይህ ጥምረትም የፍላጎትና የርዕዮተ ዓለም ጥልቅ ቅራኔ ያለበት በመሆኑ በቀላሉ የሚፈርስ ተሰባሪ ኃይል መሆኑን በውይይታቸው በአጽንኦት አስገንዝበዋል።
በአስማረ መኮንን