AMN-ሰኔ 26/2018 ዓ.ም
መንግስት በከተሞች የጀመረውን ውጤታማ የኮሪደር ልማት ወደ ገጠር በማስፋፋት፣ የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን የኑሮ ዘይቤ ለመቀየር የሚያስችል ሀገራዊ የልማት ሪፎርም እየተገበረ ይገኛል።
ይህ ታላቅ ፕሮጀክት በገጠርና በከተማ መካከል ያለውን የዕድገት ልዩነት በማጥበብ፣ የዘላቂ ብልጽግናን መሰረት ለመጣል ያለመ ሲሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጪነት ወደ ተግባር ተገብቶ በየክልሎቹ አመርቂ ውጤቶችን እያሳየ ይገኛል።
የገጠር ኮሪደር ልማት የአርሶ አደሩን አኗኗር ለማዘመንና ህይወቱን ለማሻሻል እየተተገበረ ያለ የመደመር መንግሥት ቁልፍ የለውጥ እሳቤ ነው፡፡
መሠረተ ልማትን ከማዘመን ባለፈ፣ የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ አበይት ስራዎች በተጨባጭ መሬት ላይ መታየት ጀምረዋል።

ይህ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክት የከተማ ውበትና የኮሪደር ልማት ስኬቶችን ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ በማስፋፋት፣ በአረንጓዴ አሻራ እና በሌማት ትሩፋት የተገኙ ውጤቶችን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ያለመ ነው።
የገጠር ነዋሪዎችን ከተበታተነ አሰፋፈር ወደ ተቀናጁ የገጠር መንደሮች በማምጣት ንጹህ መጠጥ ውሃ፣ መብራት፣ ጤና እና ትምህርት ቤት በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ ያደርጋል።
የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ በማልማት አካባቢውን ለቱሪዝምና ለስራ ዕድል ፈጠራ ማዕከል ወደ ማድረግ ያሸጋገራል።
ቀደም ሲል የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት ረጅም ሰዓታት በእግር ይጓዙ የነበሩ የገጠር መንደሮች፣ አሁን ላይ ደረጃቸውን በጠበቁ የጠጠርና የአስፋልት መንገዶች መገናኘት ያስቻለ ሲሆን ይህም እናቶችና ህጻናት የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሻሻልን ፈጥሯል።

ከዚህ ጎን ለጎን በኮሪደር ልማቱ አማካኝነት በሺዎች የሚቆጠሩ የገጠር አባወራዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ማግኘት የቻሉ ሲሆን፣ አማራጭ የኢነርጂ እና የፀሐይ ብርሃን መብራቶች በየመንደሮቹ በመስፋፋታቸው የገጠሩን የምሽት መልክ እየቀየረ ይገኛል።
የተተከሉ የፍራፍሬና የጓሮ አትክልቶች ከንብ እርባታ ጋር በማቀናጀት አርሶ አደሩ የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት እንዲኖረውም የሚያስችል ነው፡፡
የኢትዮጵያ የገጠር ኮሪደር ልማት የህዝብን የእለት ተእለት ህይወት ከማቅለል ባለፈ፣ በገጠርና በከተማ መካከል ያለውን የልማት ልዩነት በማጥበብ ረገድ ትልቅ ስኬት እያሳየ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ ተጠናክሮ ሲቀጥል የሀገሪቱን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ለውጥ ይበልጥ ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በሚካኤል ህሩይ