AMN- መስከረም 26/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ተጋርጠውባት የነበሩ ፈተናዎችን በፅናትና በስክነት በመሻገር፣ በሁለንተናዊ የልማትና የሰላም አዲስ ምዕራፍ ውስጥ በመግባት የታላቅነት ጉዞዋ ተፋጥኖ ይቀጥላል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።
ፕሬዚዳንቱ በሕዝብ ተወካዮች እና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪካዊ ጥበቡንና አስተዋይነቱን በመጠቀም ሀገሩን ወደፊት ለማስፈንጠር የሚያስችሉ አበይት እርምጃዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በከተሞች የተጀመሩት ውብ የኮሪደር ልማቶች ፣ የግብርና ምርታማነት ማደግና የታላቁ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንቅስቃሴዎች የሀገሪቱን የነገ ብሩህ ተስፋ የሚያመላክቱ ዋና ዋና ማሳያዎች መሆናቸውንም አመላክተዋል።

ለሀገር ሰላምና ደህንነት መስዋዕትነት እየከፈሉ ለሚገኙ የመከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ጸጥታ ኃይሎች የላቀ ምስጋናና ክብር የቸሩት ፕሬዚዳንቱ ፣ የህዝቡን ሰላም የማስከበር፣ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥና ሀገራዊ አንድነትን የማጠናከር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንገድ ሁለንተናዊ ኃይልን ማጠናከር ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ የልማትና የሰላም ድምፅ ከምንጊዜውም በላይ በሀገሪቱ ጎልቶ እንደሚሰማና የህዝቡን ብልጽግና ማረጋገጥ የሁሉም ዜጋ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።

አዲሱ የሥራ ዘመንም የኢትዮጵያን ታላቅነት ይበልጥ የሚያጎላና ውጤታማ እንደሚሆን ትልቅ ተስፋ የተጣለበት መሆኑን አረጋግጠዋል።
በታምራት ቢሻው