አዲሶቹ የትራንስፖርት ተርሚናሎች የነዋሪዎችን ሰብዓዊ ክብርና ደህንነት የጠበቁ ናቸው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- ጥቅምት 3/2019 ዓ.ም

በክረምት ወራት የተገነቡ የትራንስፖርት መሰረተ ልማቶች የነዋሪዎችን ክብርና ደህንነት የሚመልሱ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በዚህ ክረምት የተጠናቀቁት አራት ትልልቅ የተርሚናል እና የፓርኪንግ መሰረተ ልማቶች ጨምሮ ሌሎች አዳዲስ መንገዶች፣ የድሬንጅ እና የአደጋ መከላከል ስራዎች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ሰብዓዊ ክብርና ደህንነት ባረጋገጠ መልኩ ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን አስታውሰዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የበጀት ዓመቱን የ1ኛ ሩብ ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማ ማጠቃለያ የሠጡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፤ በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶች በክረምት ወራት ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል በፀሐይ ላይ ቆሞ አውቶብስና ታክሲ በመጠበቅ፣ በመገፋፋት እንዲሁም ሞባይልና ቦርሳ በመነጠቅ ይደርስ በነበረው ከፍተኛ እንግልት ይገጥመው የነበረው ሕብረተሰብ አሁን ላይ በክብር ቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ አገልግሎት የሚያገኝበት ሁኔታ መፈጠሩን ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል።

በአዲሶቹ ማዕከላት ንጽህናቸውን የጠበቁ መጸዳጃ ቤቶች፣ የምግብ እና የገበያ ቦታዎች መኖራቸውም ተገልጿል።

ከተርሚናሎቹ በተጨማሪ በየአካባቢዎቹ አዳዲስ መንገዶች፣ የእግረኛ እና የሳይክል መተላለፊያዎች እንዲሁም የድሬንጅ እና የአደጋ መከላከል ስራዎች በክረምቱ በስፋት መከናወናቸውን ከንቲባዋ አክለው ገልጸዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review