AMN – ጥቅምት 4/2019 ዓ.ም

አፍሪካ ውስጥ የከተሞች በፍጥነት መስፋፋትና የሕዝብ ቁጥር መጨመር ከሚፈጥራቸው ተፎካካሪ ፍላጎቶች ጋር ተያይዞ የመሰረተ ልማት እጥረት፣ የመኖሪያ ቤት ችግርና የአካባቢ መበከል ፈተና ሲሆኑ ይስተዋላል።
በርካታ የአህጉሪቱ መዲናዎች ለእነዚህ ውስብስብ ችግሮች አስተማማኝና ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት ጥረት በሚያደርጉበት በዚህ ወቅት አዲስ አበባ የልማትና የትራንስፎርሜሽን ተምሳሌት መሆን ጀምራለች።
አዲስ አበባ ለሁለተኛ ጊዜ ያስተናገደችው የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች አመራር ኢኒሼቲቭ (AMALI 2026) የከንቲባዎች ፎረም ተሳታፊዎች በከተማዋ የተመዘገቡትን ለውጦች ልምድ ለመለዋወጥ በመዲናዋ ተገኝተዋል።

በተለያዩ ጊዜያት አዲስ አበባን የጎበኙ አፍሪካውያን መሪዎችም የመዲናዋን የለውጥ ተሞክሮ እንደ አህጉራዊ ተምሳሌት አድንቀዋል።
ለመሆኑ የአዲስ አበባ የልማት ጉዞ የአፍሪካ ከተሞችን ትኩረት የሳበው በምን ምክንያት ነው?
አዲስ አበባ በራስ አቅም ላይ የተመሰረተ የልማት ፍልስፍና ፣ ሁለገብና የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ፣ ሰው-ተኮር ልማትና የትውልድ ግንባታ ሂደት መከተሏ ለአፍሪካ ከተሞች ተምሳሌት ሆና እንድትጠቀስ የሚያስችላት ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው።
አብዛኞቹ የአፍሪካ ከተሞች ለትልልቅ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ በውጭ ብድርና እርዳታ ላይ ጥገኛ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ይጠቀሳል። በራስ የፋይናንስ፣ የዕውቀትና የሰው ኃይል አቅም ላይ ተመሥርቶ መከናወኑ የአዲስ አበባን ተሞክሮ ልዩና ሳቢ ያደርገዋል።
ከተማዋ የውስጥ ገቢ አሰባሰብ ስርዓቷን በማዘመንና ሀገር በቀል ዕውቀቶችንና አቅሞችን በመጠቀም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በፈጣን ጊዜና በጥራት ማጠናቀቅ እንደሚቻል አሳይታለች።
ይህ በራስ አቅም መለወጥ ይቻላል የሚለው አስተሳሰብና ተግባራዊ ውጤት ለሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ትልቅ የራስ መተማመን ፈጥሯል።
አዲስ አበባን የመለወጥ ዋና ማዕከል የሆነው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ከማደስና ከማስዋብ ባሻገር ፣ በርካታ ዘርፎችን ያቀናጀና የነዋሪዎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት ያገናዘበ ሁለገብ የልማት ሥራ ነው።
የእግረኛ መንገድ፣ የብስክሌት መስመሮችና የሕዝብ ትራንስፖርት ማመቻቸት ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ አድርገዋታል።
በመዲናዋ ከመሬት ስር የሚዘረጉ የመሰረተ ልማት መስመሮች (የመብራት፣ የውሃ፣ የቴሌኮም) እና በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራሮች አገልግሎትን ቀልጣፋ አድርገዋል።
ከተማዋን ንጹህ ፣ ለኑሮና ለጤና ተስማሚ የሚያደርጉ ፓርኮችና የህዝብ መዝናኛዎች መስፋፋታቸው የከተማዋን ገጽታ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል።
አንዲት ከተማ ዘመናዊ የምትባለው የነዋሪዎቿን በተለይም የመፃኢውን ትውልድ ደህንነት፣ ትምህርትና ጤና ማረጋገጥ ስትችል እንደሆነ በባለሙያዎች ይገለጻል።
አዲስ አበባ “በአፍሪካ ህፃናትን ለማሳደግ ምርጥ ከተማ” ለመሆን የያዘችው ቁርጠኝነት የልማት ሥራዋ ሌላው ዋነኛ ማዕከል ነው።
በቅድመ-ሕፃናት እድገት ላይ ያተኮሩ ተግባራት በከተማዋ የልማት እንቅስቃሴ ቀዳሚ አጀንዳ ሆነው አርአያ የሚሆን ውጤትም ተመዝግቧል።
አዲስ አበባ ዛሬ ላይ የአፍሪካ ዲፕሎማሲያዊ መዲና ብቻ ሳትሆን የአህጉሩ ከተሞች የልማትና የትራንስፎርሜሽን ተምሳሌት ለመሆን በቅታለች።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አመራር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተቃኘውን ራዕይ ወደ ተጨባጭ የልማት ውጤት በመቀየር፣ በአፍሪካ ደረጃ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እየጻፉ ይገኛሉ።
አዲስ አበባ እውን ያደረገችው የልማት ስልት ፤ በራስ አቅም መደገፍን፣ ፈጣን አፈጻጸምን፣ የኮሪደር ልማትንና ሰው-ተኮር የትውልድ ግንባታን አዋህዶ የያዘ በመሆኑ የነገዋን አፍሪካ ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ ለሚሰሩ አህጉራዊ ከተሞች ተምሳሌት ያደርጋታል።
በታደሰ ሽፈራው