ህወሓት በትግራይ ተተኪ ትውልድ እንዳይኖር ብዙ ጥሯል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing ህወሓት በትግራይ ተተኪ ትውልድ እንዳይኖር ብዙ ጥሯል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – ጥቅምት 9/2019 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ፣ ህወሓት በንግግር ስለ ሰብአዊነት ቢሰብክም በተግባር ግን ለሰብአዊ ክብርና ሕይወት ግድ የሌለው ድርጅት መሆኑን በተለያዩ ወቅቶች በፈጸማቸው ድርጊቶች አስረድተዋል።

በትግሉ ወቅት የትግራይ ወጣቶች ፈንጂ እየረገጡ እንዲያልቁ ይደረጉ እንደነበር፣ ሀብታም የትግራይ አርሶ አደሮች ፀረ-ሕዝብ ተብለው በጉድጓድ እንደሚታሰሩና እንደሚገደሉ፣ እንዲሁም የትግራይ ነፃነት ግንባር አባላትና መሪዎች እራት ጋብዘዋቸው በተኙበት መገደላቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።

ከድል በኋላም በሺዎች የሚቆጠሩ ተጋዮች የማይጠቅሙ ተብለው ክብራቸው ተገፎ እንደተባረሩ ገልጸዋል።

ከባድመ ድል በኋላ በሃሳብ የተለዩትን አንጃዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲጋጩ መደረጉን እና የፌዴራል ስልጣን ካጡ በኋላም በ2013 ዓ.ም. ጦርነት የትግራይ ወጣቶች በጥይት መደበደባቸውንና ብዙዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን፣ አካላቸው መጎዳቱን እና በዚህ ሳምንት እንኳ ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸሙን አብራርተዋል፡፡

የድርጅቱ አባላት ማዕድን እየበዘበዙ በውጭ ሀገራት ሕንፃዎችን እንደሚገነቡ፣ መቀሌ ሄዶ ሲታይ ግን አካል ጉዳተኞች በድህነት እንደሚሰቃዩ ተናግረዋል።

ላለፉት ስምንት ዓመታት በትግራይ አንዲት የልማት ሥራ እንዳልተሰራ፣ በምትኩ ድሮንን ጨምሮ መሣሪያና ጥይት በመግዛት እንደተጠመዱ፣ በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ኮሪደሮች ሲሠሩ በትግራይ ግን ይህ የማይታወቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ሕዝቡ በከባድ ድርቅ ውስጥ እያለ ጦርነት ማወጁን፣ መንገድና የአየር መንገድ በመዝጋት ሕዝቡን ለዳግም ስቃይ መዳረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።

ህወሓት “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይበቅል” በሚል መርህ በትግራይ ተተኪ ትውልድ እንዳይኖር እና ትግራይ እንዳትኖር ብዙ ጥሯል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሆኖም ይህ እንዳልተሳካና ወደፊትም እንደማይሳካ በመጥቀስ “አህያዋ ከሞተች በኋላ ሰርዶው ይበቅላል” የሚል ጽኑ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review