AMN – ነሐሴ 16/2018 ዓ.ም
ከሐምሌ 8/2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በዛሬው ዕለት በይፋ ፍጻሜውን አግኝቷል።
በጉባኤው የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ ተገኝተው ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ የምክክር ሂደቱ ለሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ገልጸዋል።
በስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ሲመክሩ የቆዩት ከአራት ሺህ በላይ የሚሆኑ ጉባኤተኞች፣ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ የተጠናቀሩ የመጨረሻ የአጀንዳ ምክረ ሐሳቦችን በማዳመጥና በማጸደቅ ሂደቱን አጠናቀዋል።
በሀገር ግንባታ፣ በመንግሥት አወቃቀርና ቅርጽ፣ በፌዴራል ከተሞች፣ በሃይማኖት፣ በተቋማት ግንባታ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች፣ በሰላም ግንባታ እንዲሁም በሙስናና መልካም አስተዳደር አጀንዳዎች ዙሪያ ሰፊና ጥልቅ ውይይቶች ሲካሄድ መቆየቱን ምክትል ኮሚሽነሯ ተናግረዋል።
ይህ ጉባኤ በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ አለመግባባቶችንና የሐሳብ ልዩነቶችን በኃይል ሳይሆን በሰለጠነ መንገድ፣ በምክክር፣ በመደማመጥና በመከባበር ለመፍታት የሚያስችል አዲስ የፖለቲካ ባህል የታየበት ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑንም ገልፀዋል።
በጉባዔው ላይ የተገኙ የምክር ሐሳቦች ወደ ሚቀጥለው የተግባር ምዕራፍ እንዲሸጋገሩ እና ለሀገር ሁለንተናዊ እድገትና ለውጥ እንዲውሉ የሁሉንም አካላት የጋራ ትኩረትና ኃላፊነት እንደሚጠይቅ ምክትል ኮሚሽነሯ ገልፀዋል።
በበረከት ጌታቸው