AMN-ጥቅምት 17/2019 ዓ.ም
አዲስ አበባ የኪነ-ጥበብ መሠረተ ልማቷን በማስፋፋትና የጥበብ መድረኮችን ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግ፣ የከተማዋን የባህል ሕይወት ከማጎልበት ባለፈ ለባህላዊ ልውውጥና ለፈጠራ ኢኮኖሚ አዳዲስ ዕድሎችን እየፈጠረች ትገኛለች።
ባለፈው ዓመት የተመረቀው በቦሌ ፍላሚንጎ የሚገኘው ዘመናዊው የሕፃናትና ወጣቶች ቴአትርና ሲኒማ ኮምፕሌክስ የዚህ ጥረት አንዱ ማሳያ ነው።
በዚሁ ኮምፕሌክስ የሩሲያ የጃዝ ሙዚቃ ባለሙያዎች በአዲስ አበባ ቴአትርና ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር፣ በሩሲያ ኤምባሲና በፑሽኪን የባህልና የሳይንስ ማዕከል ትብብር በተዘጋጀ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ትርኢት አቅርበዋል።
ዝግጅቱ የከተማዋ የጥበብ መድረኮች ለአካባቢያዊና ለዓለም አቀፋዊ የጥበብ ልውውጦች እንዴት ሊያገለግሉ እንደሚችሉ ያሳያል።
የኪነጥበብ መሠረተ ልማት ዋና ዓላማ ሕንፃዎችን መገንባት ብቻ ሳይሆን አርቲስቶች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ለሕዝብ የሚያቀርቡባቸውን፣ ወጣቶች በጥበብ የሚሳተፉባቸውንና ማኅበረሰቡ የተለያዩ ባህሎችን የሚያውቅባቸውን ዘላቂ መድረኮች መፍጠር ነው።

እነዚህ መድረኮች የጥበብ ልምዶችን ለማጋራት፣ ለአርቲስቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የከተማዋን የባህል ቱሪዝም ለማሳደግ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
እንዲህ ያሉ የጥበብ ልውውጦች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትንና ባህላዊ ዲፕሎማሲን ከማጠናከር ባለፈ፣ ለከተማዋ ዓለም አቀፋዊ ገጽታ መጎልበትና ለቱሪዝም ዕድገት አስተዋፅኦ ያደርጋሉ።
አዲስ አበባም ያላትን የኪነጥበብ ሀብትና የተሻሻለ መሠረተ ልማት በማቀናጀት፣ ለጥበብ፣ ለባህል ልውውጥና ለፈጠራ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያግዙ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የባህል ልውውጥ ማዕከልና ተመራጭ የባህል ቱሪዝም መዳረሻ ለመሆን እየሠራች ትገኛለች።