AMN-ጥቅምት 17/2019 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ በተነገረው የአማራጭ የመምህራን ስልጠና መርሃ-ግብር ለአንድ ዓመት ያህል በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ሲሰለጥኑ የቆዩ ሰልጣኞች ተመርቀዋል።
በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያለውን የመምህራን እጥረት ይፈታል የተባለው ይህ የአማራጭ መምህራን ስልጠና መርሃ-ግብር፤ በተለያዩ የሙያ መስኮች የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸውና የመምህርነት ሙያ ላይ ፍላጎት ያላቸው እንዲሁም የተለያዩ የማጣሪያ ፈተናዎችን ያለፉ ተመልምለው የገቡበት ነው ተብሏል።
የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ተወካይ እና የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት አለባቸው ኬሚሶ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ተመራቂዎቹ በ24 የትምህርት ዘርፎች ሲሰለጥኑ የቆዩ ናቸው።
በመርኃ-ግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የትምህርት ሚኒስቴር ተወካይ ወ/ሮ አሰገድ ምሬሳ፤ ሚኒስቴሩ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል ብቁ መምህራንን ማፍራት ዋነኛው እንደሆነ ገልፀዋል። የአማራጭ መምህራን ስልጠና ደግሞ አንደኛው መሆኑንም አስታውቀዋል።
በተለይም በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት በተካተቱ አዳዲስ የትምህርት ዘርፎች ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላት መርኃ-ግብሩ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል። ስልጠናው በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ይጀመር እንጂ በሌሎች የሀገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መሰጠት መጀመሩን ገልፀዋል።

በዚህም በ2019 ዓ. ም፤ 10 ሺህ 313 ሰልጣኞች የአማራጭ የመምህራን መርሃ-ግብርን እየተከታተሉ እንደሚገኙ አስታውቀዋል። በሚቀጥሉት ዓመታት 25 ሺህ ሥክህሎት ስልጠና የሚሰጡ መምህራንን ለማብቃትም ዕቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱንም ገልፀዋል።
በዚህ የአማራጭ መምህራን መርሃ-ግብር ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ያስመረቃቸው ሰልጣኞች ቁጥር 693 ሲሆን፤ 118 የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል።
በላይሁን ፍስሃ