AMN- ግንቦት 11/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በአዘርባጃን ባኩ ከተማ ያደረገው ጉብኝት፣ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተጀመሩትን የከተማ ልማት፣ እድሳትና የቅርስ ጥበቃ ስራዎች ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል ትልቅ ልምድ የተቀሰመበት ጠቃሚ ጉብኝት መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።
ከንቲባዋ በማህበራዊ የትስስረ ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ በባኩ ከተማ የተመለከቱት አስደናቂ የከተማ እድሳት ሂደት ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ታሪክና ቅርሶችን ጠብቆ በማደስ እንዲሁም ጎስቋላ አካባቢዎችን በአዲስ መልክ በመገንባት ረገድ እያከናወነች ያለችውን ተሞክሮ የሚያንፀባርቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዳመለከቱት፣ አዘርባጃን “ጥንታዊቷ ከተማ” (The Old City) በመባል የሚታወቀውን የባኩን ክፍል በጥንቃቄ አድሳ ለጉብኝት ክፍት ያደረገች ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ ቀደም “ጥቁሯ ከተማ” (The Black City) ይባል የነበረውን አሮጌና ጎስቋላ ስፍራ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ በማፍረስና እንደ አዲስ በመገንባት፣ አዲሲቷንና ውቢቷን ከተማ “ነጭ ከተማ” (White City-Baku) በሚል ስያሜ እውን ማድረግ ችለዋል።
ይህ የባኩ ከተማ ለውጥም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተተገበረ ካለው የከተማ እድሳት ራዕይ ጋር እንደሚመሳሰል አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያም ታሪክንና ቅርሶችን ለቀጣዩ ትውልድ በማሻገር ረገድ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በፒያሳ እና በአራት ኪሎ አካባቢ ያሉ ጥንታዊ ሕንፃዎችን፣ የመጀመሪያውን ሲኒማ ቤት፣ የመጀመሪያውን ማዘጋጃ ቤት፣ ብሔራዊ ቤተ መንግሥትን እንዲሁም የተለያዩ ሐውልቶችን በተሳካ ሁኔታ ማደሷን ከንቲባዋ አስታውሰዋል።
ከዚህም ባሻገር እንደ ሐረር ጀጎል ግንብ፣ የጅማ አባጅፋር ቤተ መንግሥት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና የጎንደር ፋሲል ቤተ መንግሥት የመሳሰሉትን ታላላቅ ሀገራዊ ቅርሶች የማደስ ስራዎች በከፍተኛ ትኩረት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

የቅርስ ጥበቃ ስራው በተጓዳኝም እጅግ ጎስቋላና ለመኖር ምቹ ያልነበሩ መንደሮችን በማፍረስ ዘመናዊና ምቹ በሆነ መልኩ በድጋሚ የመገንባት ስራዎች በስፋት እየተተገበሩ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
በተለይም በቅርቡ በመዲናችን አዲስ አበባ እና በሌሎች የሀገራችን ከተሞች በተሳካ ሁኔታ የተተገበረው ሰፊ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የዚሁ የከተማ እድሳትና ማስዋብ ራዕይ ዋነኛ ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል።
ይህ ስራ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ይበልጥ ምቹ፣ ማራኪ፣ አረንጓዴ እና ዘመናዊ ለማድረግ ያስቻለ ሲሆን፣ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ከማስፋት፣ ለእግረኛና ለብስክሌት ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን ከመፍጠር እንዲሁም የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር አኳያ እጅግ አበረታችና ተጨባጭ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ከንቲባዋ በማህበራዊ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በሰፊው አብራርተዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይህ የባኩ ጉብኝት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተጀመሩትን ዘመናዊ የከተማ ልማት፣ እድሳትና የቅርስ ጥበቃ ስራዎች ይበልጥ በተደራጀና በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል የሚያስችል ጠቃሚ ተሞክሮ የተገኘበት መሆኑን በድጋሚ አረጋግጠዋል።