AMN- ጥቅምት 21/2019 ዓ.ም
በአዲስ አበባ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አገራት ከተሞችም ጭምር አርዓያ እየሆኑ ይገኛል፡፡
ከተማዋ በቅርብ ዓመታት ያከናወነችው ፈጣንና ዘመናዊ የኮሪደር ልማት፣ የሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎች፣ የነዋሪዎችን ኑሮ የሚያሻሽሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝተዋል፡፡
የአዲስ አበባ የከተማ ልማት ለውጥ የመንገድና የኮሪደር ልማት ስራዎች፣ የወንዝ ዳርቻዎች ልማት፣ የአረንጓዴ ስፍራዎች መስፋፋት፣ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የትራንስፖርት ተደራሽነት በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ የሚጠቀሱ የልማት መስኮች ናቸው።
ሥራዎቹ መዲናዋን በአጭር ጊዜ ውስጥ አስደናቂ ገፅታ ከማላበስ ባለፈ ሃብት መፍጠር የቻሉ፣ለንግድ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ እንዲሁም ለቱሪዝምና ለነዋሪዎች ማኅበራዊ ተሳትፎ አዳዲስ አማራጮችን የፈጠሩ ናቸው፡፡
የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ የልማት ስራ እና የዘላቂ የከተማ ልማት ጉዞ ለኢትዮጵያ ከተሞች ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሃገራት ከተሞችም ጭምር በአርአያነት የሚጠቀስ ነው፡፡
የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ሥራ ከተማዋን የለውጥ ምሳሌም አድርጓታል፡፡ ይሄ መልካም ተግባር አዲስ አበባ ከተማ በቻይና በተካሄደው 2026 የዓለም ከተሞች ቀን “የሸንሃይ አዋርድ” ሽልማት እንድታሸንፍ አድርጓታል፡፡
አዲስ አበባ በቻይና በተካሄደው 2026 የዓለም ከተሞች ቀን “የሸንሃይ አዋርድ” ሽልማትን ማሸነፏ ለከተማዋ ነዋሪዎች እና ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ኩራት ነው።
ዓለም አቀፍ እውቅናው ለከተማዋ ልዩ ትርጉም ያለው ሲሆን ከተማዋ ለውጭ ኢንቨስትመንትና ለዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ያላትን ማራኪነት በከፍተኛ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል። ይህ ደግሞ ለከተማዋ የኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አቅም ይፈጥራል።

እንዲሁም ከተማዋን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአካባቢ ጥበቃና ለጽዳት ትኩረት የሚሰጡ አረንጓዴ ከተሞች ውስጥ እንድትሰለፍም ያደርጋታል።
ከዚህ ባለፈም ቀጣይ የከተማዋ የልማት ፕሮጀክቶች ከዓለም አቀፍ ድርጅቶችና አጋሮች ጋር ለሚደረጉ የፋይናንስና የቴክኒክ ትብብሮች ትልቅ በር ይከፍታል።
ከተማዋ ያገኘችው እውቅና አዲስ አበባን ይበልጥ ጸዱ፣ ውብ፣ ዘመናዊና ለኑሮ ምቹ የማድረግ ጉዞ ወደፊት እንደሚቀጥል ማረጋገጫ ነው።
ይህ ድል ለአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን፣ ለመላው ኢትዮጵያ ታላቅ ኩራት መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡
ለከተማዋ ይህ የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ዕውቅና አይደለም ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በ2024 በUN-Habitat እና በደቡብ ኮሪያዋ ሴኡል ከተማ የተዘጋጀው “የሴኡል ከተማ ሽልማት” አሸናፊ መሆኗንም አስታውሰዋል።
ተከታታይ ዕውቅናዎች በከተማ ልማት የተከናወኑ ሥራዎችንና የከተማዋን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያመለክቱ ናቸው፡፡
ሰው ተኮር አቀራረብን ከከተማ መልሶ ማልማት ጋር በማቀናጀት የነዋሪዎችን ፍላጎት ቅድሚያ መስጠት፣ የትራንስፖርት አገልግሎትንና ተደራሽነትን ለማሳደግ የተወሰዱ እርምጃዎች ለዚህ ስኬት ካበቋት ዋና ዋና የልማት አቅጣጫዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
የሻምበል ምህረት
#Ethiopia#addisababa#AMN#voiceofgeneration#addismedianetwork