ከሀገራዊ ልማት እስከ አህጉራዊ ተምሳሌት የዘለቀው የኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ከፍታ

You are currently viewing ከሀገራዊ ልማት እስከ አህጉራዊ ተምሳሌት የዘለቀው የኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ከፍታ

AMN- ጥቅምት 25/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በለውጥ ጉዞዋ ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች የሀገሪቱን ብሔራዊ አንድነትና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ከማረጋገጥ አልፈው ለአፍሪካ አህጉር የሚተርፍ አዲስ የልማትና የፖለቲካ ተምሳሌት እየሆኑ ይገኛሉ።

የብልፅግና ፓርቲ ሥልጣን ከመያዙ በፊት የነበሩ አግላይ አስተሳሰቦችን ሰብሮ በማውጣት ተግባራዊ ያደረጋቸው የ”መደመር” እሳቤ፣ በራስ አቅም የተከናወኑ ታላላቅ የኢኮኖሚ ፕሮጀክቶች እና የምግብ ዋስትና ማረጋገጫዎች ሀገሪቱን አዲስ ምዕራፍ ላይ አድርሰዋታል።

ይህ ተጨባጭ እና በእጅ የሚዳሰስ ስኬት ደግሞ ከጥቅምት 26-28/2019 በአዲስ አበባ በሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ አማካኝነት ለአህጉሪቱ ለማካፈል ታሪካዊ ዝግጅት እየተደረገበት ይገኛል።

ብልፅግና ፓርቲ ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የራሱን አዲስ መንገድ ቀርጿል።

የዚህ አዲስ ልምምድ ዋና ዋና መገለጫዎች እና ተጨባጭ ማስረጃዎች መካከል፡-የ”መደመር” እሳቤና አብሮነት አንዱ ነው፡፡ ይህም ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበረውን “እኔ ካልኩት ውጪ” የፖለቲካ ባህል በማስወገድ፣ ልዩነቶችን አቀናጅቶ ለመሄድ የሚያስችል የ”መደመር” እሳቤን ተግባራዊ አድርጓል።

ይህም የተለያዩ የፖለቲካ ፍላጎቶችን በማስተናገድ ሀገራዊ አንድነትን የማጠናከር አዲስ መንገድ መኖሩን አሳይቷል።

የፓርቲዎች ውህደት እና የህብረት ባህል ሌላኛው ማሳያ ሲሆን ይህም ቀደም ሲል በቋንቋ እና በክልል ድንበር ተከፋፍለው የነበሩ ድርጅቶችን በማዋሃድ ሀገራዊ ፓርቲ መመስረቱ የፖለቲካ መበታተንን ያስቀረና የህብረት ባህልን ያዳበረ ትልቅ እርምጃ ነው።

የለውጡ መንግስት በፖለቲካው ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚውም ዘርፍ በራስ አቅም ላይ የተመሰረቱ በርካታ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን እውን አድርጓል።

የኢትዮጵያውያንን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም በግልጽ ያሳየው እና የጋራ ባለቤትነት ማሳያ የሆነው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ለሀገር ውስጥ እና ለጎረቤት ሀገራት የኃይል አቅርቦት ማዋል መቻሉ ትልቅ የድል ምዕራፍ ነው።

ሀገሪቱ የውጭ ንግድ ጥገኝነትን እንድትቀንስና የምግብ ዋስትናዋን በዘላቂነት እንድታረጋግጥ የሚያስችሏት የተፈጥሮ ጋዝ ልማት ስራ እና የማዳበሪያ ፋብሪካን የማስፋፋት ስራ በልዩ ትኩረት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በኦፓል እና በሌሎች ማዕድናት ልማት የተመዘገቡት ለውጦች የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ ላይ ይገኛሉ። በተለይም የከሰል ድንጋይን ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች እና ለተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የኃይል ምንጭነት በመጠቀም የውጭ ምንዛሪ ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ተችሏል።

የገበታ ለሸገር፤ የገበታ ለሀገር እና የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የቱሪዝም እና የተፈጥሮ ሀብት ልማትን በማስተሳሰር ሀገሪቱን ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻዎች ማድረግ ችለዋል።

በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች የተካሄዱት የኮሪደር ልማቶች ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ፣ ውብ፣ ዘመናዊ እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማዕከል አድርገዋቸዋል።

ኢትዮጵያ ከውጭ ስንዴ ማስገባቷን ሙሉ በሙሉ አቁማ ለጎረቤት ሀገራት ወደ ውጭ መላክ የጀመረችበት የምግብ ሉዓላዊነት የተረጋገጠበት ታላቅ ስኬት ተመዝግቧል።

የተተገበሩት ማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፣ የውጭ ምንዛሪ አሰራርን ዘመናዊ ማድረግ እና የኢንቨስትመንት ምህዳሩን ክፍት ማድረግ ሀገሪቱን ለውጭ ኢንቨስትመንት ምቹ አድርገዋታል።

የብልፅግና ፓርቲ አዲስ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ልምምድ ለኢትዮጵያ የልማት፣ የአንድነት እና የምግብ ሉዓላዊነት አዲስ እሳቤን ይዞ የመጣ ሲሆን አሰራሩ አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው አቅም መፍታት እንደሚችሉ ያሳየ በተጨባጭ ማስረጃ የተደገፈ ተሞክሮ ነው።

ከጥቅምት 26-28/2019 በአዲስ አበባ የሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ይህንን ሀገር በቀል ስኬት እና ሁለገብ የልማት ፍልስፍና ለአህጉራዊ ወንድሞች ለማካፈል፣ የአፍሪካን የጋራ እድገት ለማፋጠን እና የኢትዮጵያን አህጉራዊ መሪነት የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችል ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review