ኢትዮጵያ በፖለቲካ አመራር ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ ለአፍሪካ አርአያ ሆናለች- ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ

You are currently viewing ኢትዮጵያ በፖለቲካ አመራር ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ ለአፍሪካ አርአያ ሆናለች- ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ

AMN- ጥቅምት 26/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በፖለቲካ አመራርና በብሔራዊ ውሳኔ ሰጪ ተቋማት ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ ያስመዘገበችው ውጤት ለአፍሪካና ለዓለም ተሞክሮ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ የሴቶች የፖለቲካ አመራር ጉባኤ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት ሚኒስትሯ፤ ሴቶች በሀገራዊና አህጉራዊ የልማት ሂደት ውስጥ ተጠቃሚዎች ብቻ ሳይሆኑ የለውጥ መሪዎች መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ በመንግስት ካቢኔ ውስጥ 50 በመቶ የሴቶች ተሳትፎ እንዲኖር ማድረጓንና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የሴቶች ድርሻ ከ40 በመቶ በላይ መድረሱንም ጠቅሰዋል።

የመደመር ፍልስፍና የሁሉንም ዜጎች አቅም በማሰባሰብና በጋራ አስተዋጽኦ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ያብራሩት ሚኒስትሯ፤ ሴቶች በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማኅበራዊ ልማት ውስጥ እኩል ሚና እንዲኖራቸው የተቋማትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

በተጨማሪም ሴቶች በፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር፣ በዕጩ ምርጫና በውሳኔ ሰጪ መዋቅሮች ውስጥ በእኩልነት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

“የአፍሪካ ታላቁ ስትራቴጂያዊ ሀብት ሕዝቦቿ፣ የፈጠራ ችሎታቸው፣ የመቋቋም አቅማቸውና ቁርጠኝነታቸው ነው” ያሉት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፤ ሴቶች በአህጉሪቱ የወደፊት ጉዞ ውስጥ ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያስችል አካታች ሥርዓት መገንባት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ጉባኤው የአፍሪካ ሴቶችን በፖለቲካ አመራር ማብቃት፣ አካታች አስተዳደርን ማጠናከርና የፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ በሚያስፈልጉ ተቋማዊ ለውጦች ላይ ትኩረት አድርጎ እየተካሄደ ይገኛል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review