የተተከሉ ችግኞችን የጽድቀት መጠን ለመጨመር መንከባከብና መጠበቅ እንደሚገባ ተገለጸ

AMN – ሐምሌ 11/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ የወጣቶች ማኅበር “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አካሄደ። በማኅበሩ አባላትና ሠራተኞች የተከናወነው ይህ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በቦሌ ቡልቡላ መንገድ በግተራ አካባቢ ተከናውኗል።

ማኅበሩ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ላይ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን ያነሱት የመርሃ-ግብሩ ተሳታፊዎች፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሩም የዚሁ ማኅበራዊ ኃላፊነት አካል መሆኑን ገልጸዋል።

የማኅበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት ወጣት ፎሊ ንጉሴ የወጣቶች ማኅበሩ በቀጣይም በሌሎች አካባቢዎች የአረንጓዴ አሻራ ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ አክለውም፣ አባላቱ ተከላ ከማካሄድ ባለፈ የተከሏቸውን ችግኞች ተከታትሎ በመንከባከብ ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸውና ለጽድቀታቸው መትጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ ላይ የተሳተፉና ኤ ኤም ኤን ያነጋገራቸው የወጣቶች ማኅበሩ አባላት በበኩላቸው፤ የተከሏቸውን ችግኞች በባለቤትነት ስሜት በመንከባከብና በመጠበቅ የማሳደግ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ በቁርጠኝነት ገልጸዋል።

በመሐመድኑር አሊ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review