ከአምስት ዓመት ስኬቶች እስከ 2019 ትኩረቶች፡ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በጋራ ምክር ቤቶች መክፈቻ ንግግራቸው ምን ብለው ነበር?

You are currently viewing ከአምስት ዓመት ስኬቶች እስከ 2019 ትኩረቶች፡ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በጋራ ምክር ቤቶች መክፈቻ ንግግራቸው ምን ብለው ነበር?

AMN ህዳር 17/2019 ዓ.ም

7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ዛሬ ይካሄዳል።

የዛሬው ጉባኤ ዋነኛ መነሻ የሚሆነው፣ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ መስከረም 26 ቀን 2019 ዓ.ም በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ስብሰባ ላይ ያቀረቡት የመንግሥት ዓመታዊ ዕቅድ ነው።

ፕሬዝዳንት ታዬ በጋራ መክፈቻ ንግግራቸው የምክር ቤት አባላት ሥልጣን መሠረቱ የሕዝብ ድምፅ መሆኑን በማስታወስ፣ መልካም አስተዳደርን ማዘመን፣ የኑሮ ውድነትን መግታት፣ ትምህርትና ጤናን ማስፋፋት እንዲሁም ሰላምና ደህንነትን ማጽናት ቀዳሚ ትኩረታቸው ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

ባለፉት ዓመታት በግብርና፣በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና በዲጂታል መሠረተ ልማት አበረታች ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ በተለይም የ2018 ዓመታዊ የሰብል ምርት 1.3 ቢሊዮን ኩንታል መድረሱን፣ የወጪ ንግድ 11.2 ቢሊዮን ዶላር እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 4.5 ቢሊዮን ዶላር ማስመዝገባቸውን፣ የዋጋ ግሽበትም ወደ 13.4 በመቶ መውረዱን እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራና የኮሪደር ልማት ውጤቶችን በዋናነት ጠቅሰዋል።

ለ2019 ዓ.ም የሥራ ዘመን ሰላምን ማጽናት፣ ጥራትን መሠረት ያደረገ መዋቅራዊ ሽግግር ማምጣት፣ የትምህርትና ጤና ጥራትን ማሳደግ፣ የግብርናና ኢንዱስትሪ ግብዓት አቅምን ማጎልበት፣ የታክስና ዕዳ አስተዳደርን ማሻሻል፣ የፌዴራልና የክልል ቅንጅትን ማጠናከር እንዲሁም ተጽዕኖ ፈጣሪ የውጭ ግንኙነት መገንባት ዋና ትኩረቶች መሆናቸውን አብራርተዋል።

በዚህም መሠረት የኢኮኖሚ ዕድገትን 10.1 በመቶ ማድረስ፣ የዋጋ ግሽበትን ወደ ነጠላ አሃዝ ማውረድ፣ የታክስ ገቢን ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 9.62 በመቶ ማድረስ፣ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን 65 በመቶ፣ የጤና መድህን ሽፋንን 85 በመቶ እና የተማሪዎች ምገባን 70 በመቶ ማድረስ ቁልፍ ግቦች ናቸው።

ከዚህም ባለፈ የኮፕ 32 ዝግጅትን ማሳካት፣ ከ1.6 ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎችን መሳብ፣ የሀገራዊ ምክክር ምክረ ሐሳቦችን ወደ ተግባር ማስገባት እና በሰላማዊና በጋራ ጥቅም አስተማማኝ የባሕር በር እውን ማድረግ በትኩረት እንደሚሠራባቸው አመላክተዋል።

እነዚህን ግቦች ለማሳካት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጽናት፣ የጠመንጃና የግጭት ባህልን በንግግርና በመደማመጥ መተካት፣ ሙስናን መታገል፣ የተገኙ በጎ ልምዶችን ማስፋት እና የመከላከያና የጸጥታ ኃይሎችን አቅም ማጠናከር እንደሚገባ ፕሬዝዳንቱ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የሰላምና የልማት ኃላፊነት የሁሉም ዜጋ የጋራ ድርሻ መሆኑን በመግለጽ የ2019 ዓ.ም የሥራ ዘመን ውጤታማ እንዲሆን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የ2019 ዓ.ም የመንግሥት ዕቅድ መነሻ በማድረግ ከምክር ቤቱ አባላት ለሚነሡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምላሽና ማብራሪያ ይሰጣሉ።

ይህን ተከትሎም ምክር ቤቱ የመንግሥትን አቋም በማዳመጥ የድጋፍ ሞሽን ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review