AMN- ጥር 12/2017 ዓ.ም
በህገ-ወጥ ድርጊት የሚሳተፉ አካላት ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አስታውቋል።
አገልግሎቱ በማኀበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ፣ የፋይናንስ ወንጀሎች በአገር ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ዘርፈ ብዙ እና ከፍተኛ በመሆኑ ኢትዮጵያ ወንጀሎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተለያዩ ህጎችን አውጥታ በመተግባር ላይ እንደምትገኝ ገልጿል።
በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ የማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 እየተተገበረ መሆኑን መግለጫው አስታውሷል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቀድሞ በተለያዩ ህጎች ውስጥ ተበታትነው የሚገኙ የህግ ድንጋጌዎችን መሠረት በማድረግ ራሱን የቻለ የንብረት ማስመለስ አዋጅ በቅርቡ መጽደቁንም አስታውሷል።
የንብረት ማስመለስ አዋጁም ሆነ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጠጠር የወጣው አዋጅ ዓላማ የፋይናንስ ወንጀሎች አትራፊ አለመሆናቸውን በማረጋገጥ በአገር ላይ የሚያደርሰው ሁሉን አቀፍ አደጋ መግታት መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በሌላ ለጤናማ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ምቹ መደላድል መፍጠር መሆኑ ተመላክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ ግለሰቦች የወጡ ህጎችን ለማደናገሪያነት በመጠቀም እንዲሁም የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት እና የሌሎች የፀጥታ አካላትን ስም በመጥቀስ በማጭበርበር እና በማስፈራራት በህገ-ወጥ ድርጊት ገንዘብ ለማግኘት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ክትትል ማድረጉን አገልግሎቱ አስታውቋል።
በዚህም በተደራጀ አግባብ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት ውስጥ 3 ግለሰቦች ዓርብ ጥር 9 ቀን 2017 ዓ.ም እጅ ከፈንጅ ተይዘው ጉዳዩ በምርመራ ላይ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ሌሎችንም በቁጥጥር ስራ ለማዋል ከህግ አስከባሪ አካላት እየተሰራ ይገኛል ተብሏል።
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ከራሱ ምንጮችና ከጥቆማ በሚደርሱት መረጃዎች መሰረት የማጭበርበር የወንጀል ድርጊቶችን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ ወንጀሎች ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ አካላትን በህግ ተጠያቂ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።በርካታ ጉዳዮችም በህግ ተይዘው ይገኛሉ ተብሏል።
የወንጀል ድርጊት ፈጻሚዎች የህግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ አገልግሎቱ የሚወስዷቸውን ርምጃዎች የበለጠ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።
ህብረተሰቡም ማጭበርበርን ጨምሮ ሌሎች የፋይናንስ ወንጀል በመፈጸም የሚገኝን ገንዘብ ህጋዊ ለማስመሰል የሚፈጸሙ ድርጊቶችን ሲመለከት በ9796 ነፃ ስልክ ለተቋሙ ለፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በመደወል ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፏል።

All reactions:
7575