AMN – መጋቢት 9/2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ ከተማ ሀገራዊ የቱሪዝም አቅምን ማሳደግ እና ከዘርፉም የሚገኝ ጥቅምን ማላቅ የሚያስችሉ የቱሪዝም ልማት ስራዎችን እየሰራች መሆኗን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በቱሪዝም ሚኒስቴር የገበያ ልማትና ፕሮሞሽን ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ዶ/ር እንደገና አበበ ከኤኤምኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ካሏት የቱሪዝም አምቅ ሃብቶች የሚገባትን ጥቅም ማግኘት ትችል ዘንድ ከተጀመሩ የፖሊሲ አደረጃጃትና የመዋቅር ማሻሻያ ስራዎች ባሻገር በመዳረሻ ልማት ረገድ አመርቂ ስራዎች መሰረታቸውን ገልጸዋል፡፡
ከሰው ልጅ ቅደመ ታሪክ እስከ አሁናዊ የትውፊት እሴቶች ለሰማይ ከቀረበ ስነምህዳር እስከታችኛው የመሬት ጉያ ከያኔዎቹ ስልጣኔዎች እስከ ትላንት አሻራዎች ድረስ ብዙ ያላት ምድረ ቀደምቷ ሀገር ኢትዮጵያ በፀጋዎቿ ተፈጥሮ አድልቶ በሰጣት ስበቶቿ ልክ እየተጠቀመች አለመሆኑንም አውስተዋል፡፡
የትላንት ታሪክ የዘመን አሻራዎች የቅርብ ጊዜ የሀገርነት ዕድሜ ያላቸው ሀገራት ዛሬን ብቻ አልምተው ከእኛ የትላንት የታሪክ ሰበዞች የበለጠ ስለመጠቀማቸው ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ምክንያቱ ሰባት አስርተ ዓመታት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ ከዘመን የተወዳጀ ገበያን ስበትን ያላማከለ የቱሪዝም ፖሊሲና አደረጃጃቱ ዋነኛው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቱሪዝም ምቹ እንቅስቃሴ ቱሪዝም ሳቢ እይታ እንደመፈለጉ ለጎብኚዎች የተመቸ የጉዞ ምህዳር አለመኖር የመሰረተ ልማት ፈተና ሚኒስትር ዴዔታው የጠቀሷቸው ተጨማሪ ችግሮች ናቸው፡፡
ሀገር ከበዙ ጸጋዎቿ ትወዳጅ በሀብት ሳቢ መዳረሻዎቿ ልክ ትጠቀም ዘንድ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰፊ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል ይህም ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል ሚኒስትር ዴዔታው፡፡
ቱሪዝም ሀገርን አሻገሮ ወደመልካሙ መንገድ የመምራት ድርሻ ከተሰጣቸው 5 ዘርፎች ውስጥ አንደኛውን ምሰሶ ተሸክሟል፡፡ በዚሁ ጥላ ስር ፖሊሲ ክለሳና የመዳረሻ ልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከቱሪዝም እምቅ ሃብቶቿ የሚጠበቅ አበርክቶ እንድታገኝ ከማድረግ ሃገራዊ ጥረት መሳ ለመሳ በስሟና በሚጠበቅ ሃላፊነቷ ልክ ለመቆም ከጊዜ ጋር የምትሽቀዳደመው አዲስ አበባ አሁናዊ ልማቶቿ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የቀየረቻቸው መልኮቿ በርግጥም ለቱሪዝም ዘርፍ ከፍ ያለ አብርክቶ ያለው መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር እንደገና ተናግረዋል፡፡
በአቡ ቻሌ