ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ሀገር አቀፍ የስፖርት ጨዋታዎች፣ ሕዝቦችን የማስተሳሰር አቅም ያላቸው፤ የነገ የሀገር ዘዋሪ ወጣቶች ሀገራቸውንና ባህላቸውን የሚያውቁበት ዕድል የሚፈጥርበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡
“ስፖርት ለኅብረ ኢትዮጵያ አርበኝነት” በሚል መሪ ቃል በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ በጅማ ከተማ የተዘጋጀውን ስድስተኛው የመላው ኢትዮጵያ ስፖርት ጨዋታን አስጀምረናል።
መሪ ቃሉን በትክክል በምትገልጸው እና ለዘመናት የኅብረ ብሔራዊነት መናኸሪያ በሆነችው በአባ ጅፋር ሀገር ጅማ የተጀመረው የስፖርት ጨዋታ፤ ወጣት ስፖርተኞቻችን አስፈላጊ የሕይወት ክሀሎቶችን ፣ አካታችነትን፣ ፍትሐዊነትን፣ የቡድን ሥራን እና ኃላፊነትን እንዲያዳብሩ ዕድል የሚፈጥር ነው።
ስፖርት የነገዋን ኢትዮጵያ ዜጎች መፍጠሪያችን ነው፤ የነቃና የበቃ ትውልድ የምናፈራበት መስካችን ነው። ለዚህም በየአካባቢው የስፖርት ማዘውተሪያዎችን በአነስተኛ፣ በመካከለኛ እና በከፍተኛ ደረጃ እየገነባን እንገኛለን።
አንዱ አብነት ደግሞ ዛሬ ያስጀመርነውና በተለያዩ ምክንያቶች ለዘጠኝ ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ጉልህ ማሳያ ነው።
በዚህ ስፖርታዊ ጨዋታ ለተሳተፋችሁ የክልልና የከተማ አስተደዳሮች፤ የዉድድር አዘጋጅ ለሆነው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ለኦሮሚያ ክልልና ለጅማ ከተማ፣ ያለኝን ምስጋና በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ ሲሉ ገልጸዋል፡፡