እርስዎ ከሚያገኙት ገቢ ወይም ደመወዝ በወር ምን ያህሉን ይቆጥባሉ? በወር ውስጥ ለመኖር ምን ያክል ገንዘብ በቂዎት ነዉ? ኦዲቲ ሴንትራል በወር በሶስት መቶ ዩዋን ወይም 40 ዶላር ብቻ የሚኖርን ቻይናዊ ዌይዶንጊይ የተባለ የሂሳብ አስተማሪን አስተዋውቋል፡፡ ዌይ ዶንጊይንም በዚህ የቆጣቢነት የኑሮ ዘይቤው በማህበራዊ ሚዲያ ዝነኛ ከመሆኑም ባለፈ የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ስሙን አስፍሮታል፡፡
ዌይ ዶንጊይ ሰሞኑን የአለም አነጋጋሪው ግለሰብ ሆኗል፡፡የሂሳብ ሊቁን የዌይ ዶንጊን ህይወት ኦዲቲ ሴንትራል ያስነበበ ሲሆን ዶንጊ በቁጠባ ባህሉ የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ስሙን ማስፈር ችሏል፡፡
ዌይ ዶንጊይ የተወለደው በፈረንጆቹ 1991 ነው፡፡አሁን እድሜውም 33 ደርሷል፡፡ዶንጊይ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ በሂሳብ ፍቅር የወደቀ ሰው ነው፡፡
እያደገ ሲመጣም የሂሳብ ሊቅነቱ እያየለ መጥቷል፡፡ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱንም ሲጨርስ በከፍተኛ ማእረግ ነዉ፡፡ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናንም ሳይወስድ በቀጥታ የፔኪንግ ዩኒቭርሲቲን ተቀላቅሏል፡፡
ቻይና የሂሳብ ሊቆች እጥረት ባይኖርባትም ወጣቱ ዌይ ዶንጊይ ሌላው የቻይና የሂሳብሊቅ በመሆን ከእነ ኮንፊሺየስ ተራ መሰደር ችሏል፡፡ ከዩኒቨርሲቲ በማእረግ ተመርቆ እንደወጣም ወድያው በሂሳብ መምህርነት እውቀቱን ለትዉልድ እንዲያጋራ ተቀጠረ፡፡
የቁጠባ አባዜው የመጣው ከዚህ በኋላ ነው፡፡የሂሳብ ፍቅሩ ተጽእኖ ያሳደረበት ይመስልዶንጊይ በከፍተኛ ሁኔታ የቁጠባ ሱስ ውስጥ ወድቋል፡፡ራሱንም እየጎዳ የሚያገኛትን ደመወዝ እና ሽርፍራፊ ሳንቲም ሳይቀር መቆጠብ ስራዬ ብሎ ተያያዘው፡፡
ዌይ ዶንጊይ ቀስ በቀስ ፍላጎቱንም እየቀነሰ ቁጠባውንም እየጨመረ በመሄድ ከአለምቆጣቢዎች መካከል ግንባር ቀደምና በአለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ (ጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ) ላይ ስሙን ማስፈር ቻለ፡፡
ቻይናዊው የሂሳብ ሊቅ ለመኖር በወር 300 ዩዋን ወይም 40 ዶላርን ብቻ አብቃቅቶ መኖር መቻሉ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ በርካቶች እንዲከተሉት አድርጓል፡፡
ዶንጊይ ከጠዋት እስከ ማታ የሚያደርገውን የአኗኗር ዘይቤም በቲክቶክ ገጹ የሚያጋራሲሆን በርካታ እይታዎችንም በዚህ ገጹ በማግኘት ላይ ነው፡፡
በአጭር ጊዜ ውስጥም የቲክቶክ ተከታዮቹ ቁጥር ከአንዳንድ የሆሊውድና የቦሊውድ ዝነኞች ሁሉ ልቆ 90 ሚልየንን ተሻግሯል፡፡በዚህም ቻይናዊው የሂሳብ ሊቅ የበለጠ የሚቆጥበው ገንዘብ እያገኘ እንደሚገኝ ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል፡፡
በየሺዋስ ዋለ