ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሚዲያ ባለሙያዎች ጋር በነበራቸው የውይይተ መድረክ ላይ ጋዜጠኞች ዜግነትንና ብሔራዊ ጥቅምን ባከበረ መንገድ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሚዲያ የኢትዮጵያን መፃዒ ተስፋ እያሰበ በፍቅርና በአንድነት ለማንሰራራት፣ እውነትና እውቀት ሳይሸራረፉ ማንቃት ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡
ሚዲያ ጉድለት በሚታይበት ቦታ ላይ በትህትና ጥቆማ ከመስጠት እና ክፍተቱ እንዲታረም ከማድረግ በዘለለ የእውቀት ምንጭ ሊሆን እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡
መገናኛ ብዙሃን ህዝብን ማንቃት እና ማስተማር ላይ ትኩረት በማድረግ ሀላፊነታቸዉን ሊወጣ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ሲሆን መንግስትም አስፈላጊዉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡
ጋዜጠኛ ትጉ ሊሆን የተገባ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚያገኛቸው መረጃዎች ጀርባ ይበልጥ አገናዝቦና ተጨማሪ መረጃዎችን አሰባስቦ ሊያመጣ የሚችለውንም ውጤት አስቀድሞ የሚያይ ነው ብለዋል፡፡
ትጉ ጋዜጠኛ ለክስና ለወቀሳም ያልቸኮለ ሲሆን ሰነፉ ግን በተቃራኒው ነው ብለዋል፡፡
ጋዜጠኝነት ዜግነት እንደሌለው መታሰብ የለበትም : እንደማንኛውም ሙያ ዜግነት ያለው መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ጋዜጠኝነት ዜግነት፣ ብሔራዊ ጥቅም እና የሚቆምለት ሀገርና ባህል እንዳለው የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን በማሰብ ለእውነት በመቆም መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡