በአማራ ክልል ሕዝቡ ለሰላም ያለውን አቋም በድጋሚ መግለጹን ተመስገን ጥሩነህ አመላከቱ

You are currently viewing በአማራ ክልል ሕዝቡ ለሰላም ያለውን አቋም በድጋሚ መግለጹን ተመስገን ጥሩነህ አመላከቱ

AMN- ሰኔ 22/2017 ዓ.ም

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ዛሬ በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች ሕዝባዊ ትዕይንቶች ተደርገዋል፤ ሕዝቡም ለሰላም ያለውን አቋም በድጋሚ ገልጿል ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አስፍረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፣ ህዝቡ ፀረ ሰላምና ተላላኪ ኃይሎች በሚፈጽሙበት ግፍ ተማሯል ብለዋል።

በደሙና በላቡ የገነባቸው መሠረተ ልማቶች ‘የአንተ ነን’ በሚሉት የጠላት ተላላኪዎች ሲፈርሱበት በአይኑ አይቷል ያሉት አቶ ተመስገን፣ ልጆቹ ከትምህርት፣ ከብቶቹ ከግጦሽ እየተከለከሉ እጅ ከወርች ታስሮ ከርሟል ሲሉም አክለዋል።

በዚህ የተነሣ ተላላኪዎቹን ጽንፈኞች ለመታገል ቆርጦ የተነሳው ሕዝብ፣ ከዕለት ወደ ዕለት ቁጥሩ እየጨመረ መጥቷል ነው ያሉት።

በዛሬው ትዕይንተ ሕዝብ መሬቱ እስኪንቀጠቀጥ ወጥቶ ቁጣው ያስገመገመውም ለዚህ እንደሆነ ነው ያመላከቱት።

ሕዝብ ሰላም ፈልጓል ያሉ ሲሆን፣ መንግሥትም ሰላም ፈልጓል፤ ፀረ ሰላምና ተላላኪዎቹ ማን እንደሆኑ ታውቋልም ብለዋል።

ይሄንን አካል ሕዝብና መንግሥት በአንድ ግንባር ተሰልፈው፤ ገጥመው፣ በግልጽ አደባባይ አሸንፈውታል፤ ነገ ዛሬ ታይቷል በማለትም ገልጸዋል።

ተላላኪን የሚያሠማራው ላኪ ነው ያሉ ሲሆን፣ ላኪዎችን ደግሞ መንግሥትም ሕዝቡም ጠንቅቆ ያውቃቸዋል ብለዋል።

የላኪዎችን ማንነት ብቻ ሳይሆን ወቅታዊ እንቅስቃሴ እና ያሰከራቸውን የሤራ ፖለቲካም ጭምር ሕዝብ ነቅቶባቸዋል በማለት ገልጸዋል።

ላኪም ተላላኪም ከመንግሥትና ከሕዝብ በላይ አለመሆናቸውን ሊገነዘቡት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

በአደባባይ ሀቁን ላሳዩት በየደረጃው ያሉ ጀግና የአማራ ክልል አመራሮች እና ለመላው ሰላም ወዳድ ህዝብ ከፍተኛ ምስጋና አቀርባለሁም ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review