ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በይፋዊ ማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ከአንድ አመት በፊት ወደ አሶሳ መጥተን ነበር፣ ዛሬ በከተማዋ ያየነው ባለፈው አመት ካየነው በፍፁም ተቃራኒ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የተለወጠበት መንገድ ጥሩ ጅማሮ ነው ያሉ ሲሆን የኮሪደር ሥራ ውጤቱ የሚታይ ነውም ብለዋል፡፡
ከአሶሳ የተወሰኑ መቶ ኪሎሜትሮች ርቀት የሚገኘውና በማሽን የታገዘ ዘመናዊ ፋብሪካ የኩርሙክ ወርቅ ፋብሪካ አስደናቂ የሥራ ውጤት ነው። በሚቀጥለው አመት በግማሽ አቅሙ ማምረት ይጀምራል። የክልሉን ሰፊ የወርቅ አቅምም ያሳያል። ከባለፈው አመት ጉብኝታችን በኋላ ያየነው እድገት የሚበረታታ ነው። ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ በሚጠናቀቅበት ጊዜ በጎ ተጽዕኖው በመላው ክልሉ የሚታይ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
መሰል ፕሮጀክቶች ከሌሎች ፕሮጀክቶች ጋር ተደምረው የሀገራዊ ብልጽግናችን መገንቢያ ጡቦች ናቸው። ማዕድን በብዝኃ ዘርፍ የልማት ምልከታችን አንዱ ቁልፍ ዘርፍ ሆኖ ይቀጥላል። የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልልም ለዚህ ርዕይ መሳካት ዐቢይ ሚና ያለው መሆኑን እያስመሰከረ ይገኛልም ብለዋል፡፡