የተፋጠነ የልማት አጀንዳን እውን ለማድረግ ባለፉት 2 ወራት፤ ቁልፍ የሆኑ ስትራቴጂካዊ ውጥኖች፣ ግዙፍ ሀገራዊ የፕሮጀክት እና የግንባታ ሥምምነቶች ላይ በትኩረት ተሠርቷል

You are currently viewing የተፋጠነ የልማት አጀንዳን እውን ለማድረግ ባለፉት 2 ወራት፤ ቁልፍ የሆኑ ስትራቴጂካዊ ውጥኖች፣ ግዙፍ ሀገራዊ የፕሮጀክት እና የግንባታ ሥምምነቶች ላይ በትኩረት ተሠርቷል
  • የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ –

AMN – ነሐሴ 26/2ዐ17 ዓ/ም

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ በሐምሌ እና ነሐሴ ወር 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያን የተፋጠነ የልማት አጀንዳ እውን ለማደረግ ቁልፍ የሆኑ ስትራቴጂካዊ ውጥኖችን፣ ግዙፍ ሀገራዊ የፕሮጀክት አፈጻጸምን እና የግንባታ ስምምነትን ማከናወን መቻሉን ገልፀዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ወራት በ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የዩሪያ ማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ ለማቋቋም የተደረገውን ስምምነት ጨምሮ ተከታታይ ተግባራት ተከናውኗል ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በወሩ ካከናወኗቸው ቀዳሚ ተግባራት መካከል፤ ከብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባላት ጋር በመሆን አዲስ የተሠራውን ከእንጦጦ – አራት ኪሎ ፕላዛ የኮሪደር ልማት ሥራ ምረቃ ቀዳሚው እንደነበርም ገልፀዋል። አካባቢው አስደናቂ ለውጥ ያመጡ አዳዲስ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶች፣ የተሻሻሉ የመንገድ ዳር መብራቶች፣ በታዋቂው የእድ ጥበበ ገበያ በሽሮ ሜዳ የተገነቡ የዘመናዊ ሱቆችን ያካተተ ነው።

የኮሪደር ልማት ሥራው የሕፃናት መጫወቻዎች፣ ሰፊ የእግር ኳስ ሜዳ እና የተለያዩ ለሕዝብ አገልግሎት የሚውሉ ግንባታዎች የተከናወኑበትም ነው። ይህ ፕሮጀክት አስደናቂ ለውጥ ከተካሄደባቸው የመዲናዋ አካባቢዎች አንዱ መሆኑን ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት የማህበራዊ ድረ ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት የሥራ ሂደትንም ተመልክተዋል። ይኽ ሥራ አሁን በተያዘው ምዕራፍ በአምስት ክፍለ ከተሞች የሚከናወንና 21 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ፕሮጀክቱ በጥቂቱ የእግረኛ መንገዶች፣ የብስክሌት መንገድ፣ የሕዝብ ፕላዛዎች፣ የመኪና ማቆሚያዎች፣ የሕፃናት መጫወቻዎች፣ ሱቆች እና አምፊ-ቴአትሮች የተካተቱበትም ነው። በተጨማሪም የተለያዩ የአምራች ኢንዱስትሪ ተቋማትን እንቅስቃሴ እና የደረሱበትን አሁናዊ የማምረት አቅም (Production capacity) በመዘዋወር ተመልክተዋል።

ለአብነትም በሐዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ በነበራቸው ጉብኝት በፓርኩ ውስጥ የተሰማሩ ኩባንያዎች ከፀሐይ ብርሃን ኃይል ማመንጪያዎችን እያመረቱ መሆኑን የተመለከቱ ሲሆን፤ ይኽ ሥራ እሴት የተጨመረባቸው እና ሀገሪቱ ያስቀመጠቻቸውን ግቦች እና ፖሊሲዎች የሚያሳኩ ጨዋታ ቀያሪ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ከሚያደርገው የኢንቨስትመንት ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በአርባምንጭ ከተማ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክትን ጨምሮ እየተካሄዱ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተው፤ በተለይም ደግሞ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ሥራ በመጠነ ርዕዩ ግዙፍ በመሆኑ አርባምንጭ ታላላቅ ጉባኤዎችን እንድታስተናገድ ያስችላታል ነው ያሉት። ከዚህ ቀደም ከነበረን ምልከታ ሰፋ ብሎ የተከናወነው የኩልፎ ወንዝ ዳርቻ ልማት ለከተማዋ ልዩ መልኮችና ተጨማሪ ገጽታ ፈጥሯልም ብለዋል።

ወደ አርባምንጭ ጫካ አዳዲስ የመግቢያ መንገዶች የተሠሩ ሲሆን ለተራሮቹ፣ ለውሃው እና ለከባቢው ደኖች መዳረሻ ናቸው፤ የአረንጓዴ ልማት ውጤቶችን እንዲሁም አስደናቂ የፍራፍሬ እርሻ ልማት ሥራዎችን ከአርባምንጭ እስከ ወላይታ ሶዶ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወላይታ ሶዶ ጉብኝታቸው፤ አካባቢው አረንጓዴ ኢትዮጵያን የመገንባት ሀገራዊ ጽኑ ፍላጎት ምስክር መሆኑን አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በክልሉ ዋና ከተማ አሶሳ እና አከባቢ ያለውን የኮሪደር ልማት ሥራ እና የኢንዱስትሪ ልማት እንቅስቃሴዎች ያስገኙትን ተጨባጭ ለውጥ የተመለከቱ ሲሆን፤ ከአሶሳ የተወሰኑ መቶ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የሚገኘውን የኩርሙክ ወርቅ ፋብሪካ አስደናቂ የሥራ ውጤትንም ተመልክተዋል። ማዕድን በብዝኃ ዘርፍ የልማት ምልከታችን አንዱ ቁልፍ ዘርፍ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልልም ለዚህ ርዕይ መሳካት ዐቢይ ሚና ያለው መሆኑን እያስመሰከረ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።

ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በአካል ተገኝተው ለመመልከት ባደረጉት ተከታታይ እንቅስቃሴ፤ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውን ጨምሮ ከከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመሆን የተጠናቀቀውን የአለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል-ጎሮ-ቪአይፒ ኮሪደር ተመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ የመደመር ሐሳብ ላይ የጻፉት አራተኛውንና “የመደመር መንግሥት” የተሰኘውን አዲስ መጽሐፍን በተመለከተ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የመጽሐፉ ሐሳብ የወልና ገዥ እንዲሆን የሚያስቸሉትን በርካታ ሂደቶችን ያለፈ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፣ የመደመር ፍልስፈናና እሳቤ የጠራ እና በሰፊው ተቀባይነት ያለው የአስተዳደር ሞዴል፣ የኢትዮጵያን ሀገራዊ ትልምን የቀረፀ እና የህዝብ አመኔታ የተረፈ ነው። በሌላ በኩል ለኢትዮጵያ ግብርና ሽግግር ትልቅ እጥፋት እንደሆነ በታመነው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና የዳንጎቴ ግሩፕ በጎዴ አካባቢ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የዩሪያ ማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ ለማቋቋም የውል ስምምነት ተደርጓል።

2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የሚፈስበት ይህ ፕሮጀክት በአመት እስከ ሶስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የማምረት አቅም የሚኖረው ሲሆን በአለም ከግዙፎቹ ፋብሪካዎች ተርታ የሚመደብ ይሆናልም ብለዋል። በአርባ ወራት እንዲጠናቀቅ እቅድ የወጣለት ፕሮጀክት በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን የሥራ እድል የሚፈጥር ሲሆን፤ ኢትዮጵያን ከውጭ ከማስመጣት ጥገኝነት ነፃ በማውጣት የቀጠናው የማዳበሪያ ምርት ማዕከል ያደርጋታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሐምሌ እና ነሐሴ ወር 2017 ዓ.ም ከፍተኛ የሆነ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች አፈጻጸምን በሚመለከት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመዘዋወር ምልከታ ያደረጉበት እና የፕሮጀክቶች እንቅስቀሴ እንዲፋጠን በአካል ተገኝተው አቅጣጫ ያስቀመጡበትም ስኬታማ ወር እንደነበር ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት የማህበራዊ ድረ-ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review