የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት በተሳካ መልኩ እንዲከበሩ ፖሊስ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ወደ ተግባር መግባቱን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ገለፁ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ዘንድሮ ከአዲስ ዓመት ዋዜማ ጀምሮ የኢትዮጵያን ከፍታ ያሳዩ በርካታ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች እየተስተናገዱ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአብነትም ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ፣ የአፍሪካ የካረቢያን ጉባኤ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ምረቃ እና ምረቃውን አስመልክቶ የተካሄዱና እየተካሄዱ የሚገኙ የደስታ መግለጫ ሰልፎች ያለምንም ስጋት በስኬት መቀጠላቸውን አንስተዋል።

ለዚህም የፖሊስና የሌሎች የፀጥታ ተቋማት ሚና የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል። በመስከረም ወር ሕዝብ በስፋት ወደ አደባባይ በመውጣት ከሚያከብራቸው በዓላት መካከል የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት በተከታታይ እንደሚከበሩ አመልክተው፤ ለዚህም ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
የመስቀል ደመራ በዓል በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢ በድምቀት የሚከበር የአደበባይ በዓል መሆኑን ጠቅሰው፥ በዓሉ ሃይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ፖሊስ በቴክኖሎጂ የታገዘ ዝግጅት ማድርጉን አስታውቀዋል።
በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የመስቀል ደመራ በዓል ላይ ለመታደም የሚገኙ ቱሪስቶች ሰላምና ደህንነታቸው ተጠብቆ የቆይታ ጊዜያቸው ያማረ እንዲሆን አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በተመሳሳይ በርካታ ህዝብ በአዲስ አበባና በቢሾፍቱ የሚታደምበት የኢሬቻ በዓል በተሳካ መልኩ እንዲከበር ፖሊስ አስፈላጊውን ዝግጅት አደርጓል ነው ያሉት።
በአዲስ አበባና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚደረጉ ታላላቅ ሀገራዊና ህዝባዊ ሁነቶች እና በዓላት በድምቀት መካሄድ ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።