በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የሊግ ምዕራፍ 4ኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬም ሲቀጥሉ ማንችስተር ሲቲ ከ ቦሩሲያ ዶርትመንድ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
ሁለቱ ክለቦች ከሦስት ጨዋታ በተመሳሳይ ሰባት ሰባት ነጥብ ሰብስበዋል።ማንችስተር ሲቲ እና ዶርትመንድ በቻምፒየንስ ሊጉ እርስ በእርስ ሲጫወቱ ለሰባተኛ ጊዜ ይሆናል።
ከዚህ ቀደም ባከናወኑት ስድስት ጨዋታ ሲቲ ሦስቱን አሸንፏል። የጀርመኑ ክለብ ደግሞ አንዱን ብቻ በድል ተወጥቷል። አስደናቂ የግብ ማግባት ሂደት ላይ የሚገኘው ኧርሊንግ ብራውት ሃላንድ የቀድሞ ክለቡ ዶርትመንድን ይገጥማል።
ኖርዌያዊው አጥቂ በተመሳሳይ ከሁለት ዓመት በፊት ዶርትመንድን ገጥሞ ግብ ማስቆጠሩ ይታወሳል። በሌሎች ጨዋታዎች ባርሰሎና ከሜዳው ውጪ ክለብ ብሩጅን ይገጥማል።
ኒውካስትል ዩናይትድ አትሌቲክ ቢልባኦን ሲያስተናግድ ፣ ኢንተር ሚላን ለውድድሩ አዲስ የሆነውን የካዛኪስታኑን ኪራት አልማቲን ይገጥማል። ማርሴይ ከአታላንታ ፣ ቤኔፊካ ከ ባየር ሊቨርኩሰን እንዲሁም አያክስ ከ ጋላታሳራይ ሌሎች የምሽቱ ጨዋታዎች ናቸው።
ሁሉም ምሽት 5 ሰዓት ሲል የሚጀምሩ ይሆናል። ከእነዚህ ጨዋታዎች ቀደም ብሎ ካራባግ ከቼልሲ እና ፓፎስ ከ ቪያሪያል ጨዋታቸውን ምሽት 2:45 ላይ ይጀምራሉ።
በሸዋንግዛው ግርማ