ኢትዮጵያ በብልጽግና ጉዞ ላይ ለመሆኗ በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ማሳያ ናቸው

You are currently viewing ኢትዮጵያ በብልጽግና ጉዞ ላይ ለመሆኗ በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ማሳያ ናቸው

‎AMN – ህዳር 12/2018 ዓ.ም

‎ኢትዮጵያ በብልጽግና ጉዞ ላይ ለመሆኗ በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ማሳያ ናቸው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር ገለጹ።

‎20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ህዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ ከተማ አቀፋዊ የህዝብ ለህዝብ መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

‎በመድረኩ ከተለያዩ ክልሎች የተወጣጡ የብሔር ብሔረሰብ ተወካዮች፣ የሀይማኖት አባቶች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

‎በዚሁ ወቅት መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር፣ አዲስ አበባ የሁሉም ብሄሮች እና ህዝቦች መገኛ በመሆኗ በዓሉ ልዩ ትርጉም ይሰጠዋል ብለዋል።

‎ያለፉት የለውጥ አመታት በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊ እና በፖለቲካዊ ዘርፎች እምርታዎች የተገኙበት መሆኑን የጠቆሙት አፈ ጉባዔዋ፣ በእነዚሁ የለውጥ ዓመታት አካታች የሆነ እውነተኛ የፌዴራሊዝም ስርዓት ተፈጥሯል ብለዋል።

‎ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች በሁሉም አካባቢ መዳረሳቸው የዚሁ እምርታ ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።

‎ልማት የጋራ ጥረትን እንደሚፈልግ የጠቆሙት ወይዘሮ ቡዜና፣ ለመጻኢ የሀገር እጣፈንታ ሁሉም በመሳተፍ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

‎ያለፉት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ በትክክለኛ የብልጽግና ጉዞ ላይ መሆኗን የገለጹት አፈ ጉባኤዋ፣ ለዚህም አዲስ አበባ ዋነኛ ማሳያ ነች ብለዋል፡፡

‌‎የአዲስ አበባ ከተማ ትልቅ እምርታ ማሳየቷን ያመላከቱት አፈ ጉባኤ ቡዜና፣ በከተማዋ የብሔር ብሔረሰቦችን ውክልና በማረጋገጥ በኩልም ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን አክለዋል።

‎20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔሰሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል “ደሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ በሆሳዕና ከተማ ይከበራል።

‎በሀብታሙ ሙለታ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review