AMN- ሰኔ 5/2018 ዓ.ም
ካናዳ የ23ኛው ዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ከሆኑ ሶስት ሀገራት አንዷ ናት።
ሀገሪቱ የተሻለ ውጤት ያመጡልኛል ብላ ከያዘቻቸው 26 ተጫዋቾች አንዱ ኢትዮጵያን ያስጠራል። በካናዳ እትብቱ ቢቀበርም የዘር ሀረጉ ከኢትዮጵያ ይመዘዛል፤ የ25 ዓመቱ ዓሊ አፈንዲ አሕመድ።
ዓሊ አፈንዲ፣ አፈንዲ እና ሙና ከተባሉት ኢትዮጵያውያን ወላጆች የተገኘ እግርኳስ ተጫዋች ነው። ቤተሰቦቹ በኢትያጵያ በሀረርጌ ዞን በዴሳ ከተማ ይኖሩ የነበሩና መጀመሪያ ወደ ጣልያን ከዛም ወደ ካናዳ ያቀኑ ናቸው።

በቶሮንቶ የተወለደው ዓሊ አሕመድ፣ ለእግርኳስ የተለየ ፍቅር የያዘው በቤተሰቡ ምክንያት ነው። በጣልያን መኖራቸው ለሴሪ አ የተለየ ፍቅር እንዲይዙ ያደረጋቸው የዓሊ ቤተሰቦች፣ ልጃቸው በእግርኳስ ፍቅር እንዲነደፍ አድርገዋል።
ዓሊ ተሰጥኦ ቢኖረውም ፕሮፌሽናል እግርኳስ ተጫዋች ለመሆን ግን በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል። በቅድሚያ በከፊል ፕሮፌሽናል ለሆነው ሰሜን ቶሮንቶ ኒትሮስ ከዛም ለዋይትኬፕስ አካዳሚ ተጫውቷል።
ቀጥሎ የእግርኳስ ሕይወቴን አቀናለሁ ብሎ በ17 ዓመቱ ወደ ፖርቹጋል አቅንቶ እንደነበር በቅርቡ ከሲቲቪ ኒውስ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል። ፖርቹጋል ግን እጇን ዘርግታ አልተቀበለችውም፤ ውሉ ጠፍቶበት ወደ ካናዳ ለመመለስ እንደተገደደ ዓሊ በአንደበቱ ገልጿል።
በመስመር አማካይነት የሚጫወተው ዓሊ አሕመድ፣ በቫንቾቨር ዋይትኬፕስ ያሳለፈው ሶስት ዓመታት ለብሔራዊ ቡድኑ እንዲመለመል አድርጎታል። በተያዘው ዓመት 2026 ጥር ወር ላይ በእንግሊዝ ሁለተኛ ዲቪዚዮን (ቻምፒየን ሺፕ) ለሚወዳደረው ኖርዊች ሲቲ መፈረሙ የበለጠ ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ በሩን ከፍቶለታል።

የትውልድ ሀገሩ ካናዳን ከ2023 ጀምሮ የወከለው ዓሊ፣ በሰሜን አሜሪካ ኔሽንስ ሊግ፣ በጎልድ ካፕ እና ኮፓ አሜሪካ ውድድሮች ላይ የስብስቡ አካል ሆኖ ተጫውቷል። አሁን ደግሞ በትልቁ መድረክ ዓለም ዋንጫ ላይ ካናዳን እንዲወክል ተመርጧል።
በዓለም ዋንጫ መሳተፍ ያለውን ስሜት ለመግለፅ እንደሚከብድ ለሲቲቪ ያነሳው ዓሊ፣ ምንም እንኳን ካናዳዊ ቢሆንም ለኢትዮጵያ የተለየ ፍቅር እንዳለው ተናግሯል።
ዓሊ አፈንዲ አሕመድ ካናዳ ከቦስኒያ ሄርዞጎቪና በሚያደርጉት የ2026 የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ግጥሚያ ላይ ኢትዮጵያዊ የዘር ሀረጉን ይዞ ለካናዳ ብሔራዊ ቡድን ይጫወታል።
በሸዋንግዛው ግርማ