በአፍሪካ የሚፈፀሙ ኢ-ህገ መንግስታዊ የመንግስት ቅየራዎች በየትኛውም መንገድ ሊወገዝ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ ተናገሩ፡፡
4ኛውን የአፍሪካ ሕገ-መንግስታዊ ፍርድ ቤቶችና መሰል ተቋማት ዓለም አቀፍ ሲምፖዚየም በአፍሪካ ህብረት እየተካሄደ ነው።
ሲምፖዚየሙ እየተካሄደ ያለው “ሕገ-መንግስታዊነትና ሀገረ መንግስት ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ ሲሆን፣ በሲፖዚየሙ ላይ የአባል ሀገራቱ የሕገ-መንግስታዊ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝደንቶች፣ በዓለም አቀፍ ተቋማት የሚሰሩ የዘርፉ ምሁራን እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ይገኛል።

በሲምፖዚየሙ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴ፣ ኢትዮጵያ ህገ መንግስታዊ ስርዓት እንዲሰፍን በተለያዩ ዘመናት መስራቷን የገለፁ ሲሆን፣ ህገ መንግስታዊነት እንዲረጋገጥም ተቋማትን የማጠናከር ስራ እየሰራች ነውም ብለዋል።
በአፍሪካ ህገ መንግስታዊነት እንዲረጋገጥ እና የተሻለ የመንግስት ስርዓት እንዲገነባ አፍሪካዊያን ቁርጠኛ ሊሆኑ ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንት ታየ፣ በአህጉሪቱ የሚፈፀሙ ኢ-ህገ መንግስታዊ የመንግስት ቅየራዎች በየትኛውም መንገድ ሊወገዝ ይገባልም ብለዋል።
በአፍሪካ ጠንካራ የመንግስት ስርዓት ለማስፈን የጋራ ስራ ያስልጋል ሲሉ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ በተወካያቸው በኩል ተናግረዋል።
በዚህ ሲምፖዚየም ኢትዮጵያ ተሞክሮዋን እንደምታካፍልና በዘርፉ የተደረጉ በርካታ የምርምር ውጤቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተነግሯል።
በአሰግድ ኪዳነማሪያም