በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ በተካሄደው ሦስተኛው የኢጋድ መገናኛ ብዙኃን የሽልማት ሥነ-ሥርዓትን የከፈቱት የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ጋዜጠኞች በቀጠናው ያለውን እውነታ፣ የመቋቋም አቅምና የሰላም ተስፋ በማንፀባረቅ የሚጫወቱት ወሳኝ ሚና የላቀ መሆኑን ገለጹ።
ዶ/ር ወርቅነህ “አንዳንድ ምሽቶች አሉ የጠቅላላውን ቀጠና ተስፋና ክብደት የሚሸከሙ፤ ዛሬ ደግሞ ከእነዚያ ብርቅዬ አጋጣሚዎች አንዱ ነው” ብለዋል።
የኢጋድ ዋና ጸሐፊው ሽልማቱ “የታሪክ ነጋሪዎች”፣ “ጋዜጠኞች” እና “የይዘት ፈጣሪዎች” የአካባቢውን ድምጾች በድፍረት፣ በእውነት እና በጽናት የሚያሰሙት የጋራ ታሪካችን ጠባቂዎች ለማክበር ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።

የዘንድሮው መድረክ በዋናነት “የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃ”፣ “ሰላምና ደህንነት”፣ እና “የምግብ ዋስትና” ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። እነዚህ ጉዳዮች ለአፍሪካ ቀንድ ‘የቀጠናው የልብ ምት’ የሆኑ አጀንዳዎች እንደሆኑ ዋና ጸሐፊው አስምረውበታል።
ዶ/ር ወርቅነሁ የአየር ንብረት ለውጥ የቀጠናውን ተግዳሮቶች የሚያባብስ ጉዳይ መሆኑን ገልጸው በሶማሊያ የተከሰተውን ጎርፍ፣ በኢትዮጵያ፣ በኬንያና በሶማሊያ የተከሰተውን ድርቅ፣ እንዲሁም በሱዳን ያለውን ጦርነትና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ውድመት በአስረጅነት አቅርበዋል።
በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ከ40 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የኢጋድ አባል ሀገራት ዜጎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን አስረድተው፣ ይህን ለመሰሉ አስቸኳይ ሁኔታዎች ጋዜጠኞች ድምጽ እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
#ኢጋድመገናኛብዙኃን (IGAD Media)
#ኢጋድሽልማት (IGAD Award)