ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራትን የጋራ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው

You are currently viewing ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራትን የጋራ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው

AMN ሕዳር 23/2018

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን እና የዓባይ ተፋሰስ ሀገራትን የጋራ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ እንደሚገኝ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ የኃይል ማመንጫ ግድቦች የውሃ አስተዳደር በዕውቀትና በከፍተኛ ኃላፊነት የሚመራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም የሀገራት መሪዎች፣ የቀጣናዊ፣ አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት መመረቁ ይታወቃል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)÷ የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ስኬት ለዘመናት የልማት ቁጭት መልስ የሰጠ የኢትዮጵያውያን የአዲስ ዓመት የብሩህ ተስፋ ብስራት ነው ብለዋል።

ከግድቡ የሚገኘው ኃይል የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር በማሳለጥና ቀጣናዊ የኃይል ትስስርን በማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው የፈጠረችው ከፍተኛ የኃይል ትስስር የአፍሪካን የኢኮኖሚ ውህደት ለማረጋገጥ የራሱን መሰረት መጣሉን ተናግረዋል።

የሕዳሴ ግድብ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት የሚከሰተውን ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ በመቀነስና በበጋ ወራት አስተማማኝ የውሃ ፍሰት በማስገኘት ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ መሆኑን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል በግብጽ አማካይነት በአንድ በኩል ውሃ ተያዘብን በሌላ በኩል ጎርፍ ተለቀቀብን በሚል የሚናፈሱ መረጃዎች እርስ በርስ የሚጣረሱና መሰረተ ቢስ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ የኃይል ማመንጫ ግድቦች የውሃ አስተዳደርና ውሃ አለቃቀቅ ሥርዓት በዕውቀትና በከፍተኛ ኃላፊነት እየተመራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የሕዳሴ ግድብ የውሃ አስተዳደር የኢትዮጵያን ጥቅም በማስከበር የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራትን በማይጎዳ መንገድ በብሔራዊ ቴክኒካል ኮሚቴ እየተመራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ስንገነባ እኛን ለመጉዳት ነው ሲሉ የነበሩ አካላት ግድቡ እውን ከሆነ በኋላ አካሄዳቸው ከፍተኛ ውሃ እየተለቀቀብን ነው ወደሚል ሀሰተኛ ትርክት ተቀየረ ሲሉም ገልጸዋል።

ሕዳሴ ግድብ የዓባይን ውሃ በተገቢው መንገድ በማስተዳደር የኢትዮጵያንና የታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በውሃ ሃብቷ እንዳትጠቀም ለዘመናት ሲሸረብባት የነበረውን ሴራና ትርክት በመቀልበስ የጋራ ተጠቃሚነት መርህን ማስረጽ እንደቻለች ተናግረዋል።

በኢትዮጵያውያን አንጡራ ሃብት የተገነባውን ሕዳሴ ግድብን በጋራ እናስተዳድር የሚል ሉዓላዊነትን የሚዳፈር የቅዠት እሳቤም ተቀባይነት የሌለው አካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህ የምትገዛ ሀገር ናት ያሉት ሚኒስትሩ፤ ግብጽና ሱዳን በዓባይ ውሃና በሕዳሴ ግድብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የጸና አቋሟን በተግባር እያሳየች ነው ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review