ኢትዮጵያ 2ተኛውን የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ እንድታስተናግድ ተመረጠች

You are currently viewing ኢትዮጵያ 2ተኛውን የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ እንድታስተናግድ ተመረጠች

AMN – ሰኔ 11/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ በአፍሪካ አስተዳደር ማዕከል የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ኢኒሼቲቭ በየዓመቱ የሚካሄደውን ጉባኤ ለማካሄድ ተመርጣለች፡፡

ጉባኤው “ለእድገት ማስተዳደር፡ ፖለቲካ ፓርቲዎች የአፍሪካ የወደፊቱ ኢኮኖሚ ቀራጺዎች” በሚል መሪ ሐሳብ ፣ በ2019ዓ.ም ጥቅምት ወር ላይ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

ጉባኤው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች በመላ አህጉሪቱ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርን በማስፋት ፣ ተቋማትን በማጠናከር እና ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን በመምራት ያላቸውን ቁልፍ ሚና አጽንኦት በመስጠት የሚካሄድ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ምርጫ የዲሞክራሲያዊ መሻሻልን ፣ ኢኮኖሚያዊ ለውጥን እና ብሄራዊ ልማትን በማስፋት ረገድ የፖለቲካ ፓርቲ ተቋማት ያላቸውን ሚና አህጉራዊ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን የሚያመላክት መሆኑ ተገልጿል፡፡

የመጀመሪያው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ በጋና አካራ ነበር ከዓመት በፊት የተካሄደው፡፡

ለሁለተኛው ጉባኤ ዝግጅት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዘዳንት አደም ፋራህ ፣ የአፍሪካ አስተዳደር ማዕከል ሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ሊቀ መንበር ቤኔዲክታ ላሲን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በውይይታቸው አደም ፋራህ አፍሪካውያን ባለቤት የሆኑበት አውድ መፈጠሩ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ገንቢ ንግግርን ለማከናወን እና ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርን ለማጠናከር ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ጉባኤው በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድም በትብብር ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋጠዋል፡፡

በጉባኤው የሀገራት መሪዎች ፣ ፖሊሲ አውጪዎች ፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ፣ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች ፣ የሲቭል ማሕበራት እና የልማት አጋሮች እንደሚታደሙበት ከብልጽግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review