ኢትዮጵያ የብዝኃ ባህል፣ ወግ፣ ልማድ እና የጥንታዊ እሴቶች ባለቤት ናት። ታዲያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለዘመናት በማኅበረሰቡ ዘንድ ተከብረው የቆዩ የአለባበስ ሥርዓቶች “ፋሽን” በሚል ስም ከባህላዊ እሴቶቻችን ጋር እየተጋጩ፣ ማኅበረሰቡን በማይመጥንና በማይወክል ደረጃ ወርደው የመምጣት ዝንባሌ መታየት ጀምሯል። ይህ አዝማሚያ ከግለሰቦች አልፎ በብዙኃን መገናኛ (ሚዲያ) ላይ መታየቱ “ወዴት እየሄድን ነው?” የሚል ትችትና ቁጭት እየፈጠረ ይገኛል።
የትውልድ ድምጽ የሆነው አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ባሕልና ወግ ልማዱን የጠበቀ ትውልድ ለማፍራት በትኩረት ይሠራል፤ ለዚህም የተለያዩ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
የሕግ ማስከበር ሥራዎች ምን ያህል ሕጋዊ መሠረት አላቸው?
በሰሞኑ አጀንዳ ላይ ስለሆነው ከባህል ያፈነገጠ አለባበስ ጋር በተያያዘ እየተወደሱ ያሉ የሕግ ማስከበር ሥራዎች ከሃገሪቱ ሕግ አንፃር ምን ያህል አንደምታ አላቸው? ሲል AMN 24/7 የሕግ ባለሙያ ማብራሪያ ጠይቋል።

የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ስሜነህ ተክሉ፣ ከባህል ያፈነገጠ አለባበስ ከሃገሪቱ ሕግ አንፃር እንዴት እንደሚታይ፣ ሕጉ ምን እንደሚል እንዲሁም ቅጣቱ ምን እንደሆነ በዝርዝር አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 639 ስር “መልካም ሥነ-ምግባር እና መልካም ተግባር ተቃራኒ የሆነ የብልግናና አሳፋሪ ሥራን በአደባባይ መፈጸም” በሚለው ክፍል ውስጥ፣ ከባህል ያፈነገጡ አለባበስን በተመለከተ የሚገልጽ አንቀጽ መኖሩን አቶ ስሜነህ አረጋግጠዋል።
ማንኛውም ማኅበረሰብ የመልካም ሥነ-ምግባር መለኪያዎች አሉት።
ከእነዚህ በተቃራኒ የሚያደርጉ ሰዎችን መቅጣትና ሥራቸውንም ማስቆም የሕጉ ዋነኛ ዓላማ መሆኑን አብራርተዋል።
⚖️ በሕገ-መንግስቱም ሆነ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 639 ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ፣ ጥፋተኛው ለአካለ መጠን ባልደረሰ ልጅ ፊት ድርጊቱን የፈጸመ እንደሆነ ቅጣቱ የበለጠ ከባድ መሆኑን ያሳያል። በተለይ ሕፃናትን የሚመለከት ወይም የሚጎዳ ድርጊት ከሆነ ደግሞ ቅጣቱ ከፍ ያለ መሆኑን ሕጉ ይደነግጋል ብለዋል።
ስለሆነም ከባህል ያፈነገጡ ተግባራት እንዳይከናወኑና ተከናውነው ሲገኙም ለመቅጣት ሕጉ ሙሉ በሙሉ የሚፈቅድ መሆኑን የሕግ ባለሙያው ገልጸዋል።
ምን ይደረግ?
አቶ ስሜነህ፣ ማኅበረሰቡ መልካም ሥነ-ምግባር እና ጠባይ የሚላቸው እሴቶች አሉትና ከእነዚህ ወጥቶ መፈጸም ወይም ማፈንገጥ ማለት ፀረ-ማኅበረሰብ መሆን ወይም ከማኅበረሰብ ተቃርኖ መሄድ ማለት ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ስለዚህም ድርጊቱን ለመፈጸም “ዴሞክራሲያዊ መብቴ ነው” ማለት አግባብ አለመሆኑን እና መሰል ድርጊቶችን የሚከላከል ሕግ እንደ ሃገር መኖሩን የሕግ ባለሞያው አቶ ስሜነህ ተክሉ ገልጸዋል።
(በያለው ጌታነህ)