የአዲስ አበባ የመስሪያ ቦታዎች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ አገልግሎቱን በዘመናዊ መንገድ ለመስጠት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ይፋ አድርጓል።
የአዲስ አበባ የመስሪያ ቦታዎች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ለኢንተርፕራይዞች የመስሪያ ቦታን በማመቻቸትና በማልማት ረገድ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
በመሆኑም ኢንተርፕራይዞች ባሉበት ሆነው መረጃና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ወደ ስራ አስገብቷል።
የቴክኖሎጂ ይፋ ማድረጊያ መርሀ ግብሩን በንግግር የከፈቱት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀምበር (ዶ/ር)፤ በአሁኑ ጊዜ የከተሞችና የተቋማት ማደግና መዘመን የሚወሰነው ቴክኖሎጂ አጠቃቀም መሆኑን ገልጸዋል።
በዲጅታል ኢትዮጵያ ጉዞ በአዲስ አበባ የሚገኙ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዘዉ የሚነሱ ቅሬታዎችን በመቅረፍ የአገልግሎት አሠጣጡን ማዘመን ላይ እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይም ተቋማት አሰራራቸውን በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ይሰራል ያሉት ጀማሉ ጀምበር (ዶ/ር)፤ ከመስሪያ ቦታዎች ዙሪያ በተደጋጋሚ የሚነሱ ቅሬታዎችን እንዲሁም ያሉ የመስሪያ ቦታዎችን የመለየትና የአገልግሎት ጊዜያቸውን የመቆጣጠር ስራውን እንደሚጠናከር ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ የመስሪያ ቦታዎች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አይዳ አወል በበኩላቸው፤ ቴክኖሎጅው የተጠቃሚውን እርካታ ለማረጋገጥና የአዲስ አበባን የስማርት ከተማነት ጉዞ የሚያፋጥን መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ተገልጋዩ ባለበት አገልግሎት በማግኘት የጊዜ ብክነትን የሚቀንስና አስፈላጊውን መረጃ በፍጥነት የሚያደርስ ስለመሆኑ ገልፀዋል።
የኢንተርፕራይዝ ባለቤቶች የለማውን ቴክኖሎጂ በባለቤትነት ስሜትና በኃላፊነት በአግባቡ በመጠቀም አስፈላጊውን መረጃ ማግኘት አለባቸው ብለዋል ።
ወደ አገልግሎት የገባው ቴክኖሎጂ 8 ዋና ዋና አገልግሎቶችንና 13 ንዑሳን አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ ተገልጷል።
ቴክኖሎጂው ይፋ ማድረጊያ መርሀ ግብሩ ላይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀምበር (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻዎች ተገኝተዋል።
በንጉሱ በቃሉ