AMN-ሰኔ 8/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በ2018 የትምህርት ዘመን ያከናወናቸው ተግባራት፤ ከተማዋ የደረሰችበትን እድገት የሚመጥን እና ከዚህ ቀደም የነበሩ የትምህርት ስርዓት ስብራቶችን መጠገን የቻሉ መሆናቸውን በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታውቋል።
ቋሚ ኮሚቴው በትምህርት ቢሮው የተከናወኑ ቁልፍና አበይት ተግባራት አፈጻፀምን መሰረት ያደረገ የመስክ ሱፐርቪዥን አካሂዷል።

ቋሚ ኮሚቴው በትምህርት ቢሮው ከትግበራ እስከ ማጠቃለያ ምዕራፍ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት አፈጻፀም ሪፖርትን ያደመጠ ሲሆን፣ በገላን ጉራ አዳሪ ትምህርት ቤትም በመገኘት የስራ እንቅስቃሴዎችን ተመልክቷል።
ቢሮው በየጊዜው እያደገ የመጣ ተቋማዊ አሰራር ስርዓት መዘርጋቱ፣ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ያደረጋቸው ጥረቶች፣ የተቋማትን ስታንዳርድ ማስጠበቁ እንዲሁም የትምህርት ቤት ማስፋፊያ ግንባታዎችን በከፍተኛ ፍጥነት ማከናወኑ የሚደነቁ መሆናቸውን ቋሚ ኮሚቴው በግምገማው ጠቅሷል።

በመድረኩ ላይ በርካታ ስኬታማ ተግባራት መኖራቸው ቢገለጽም፤ የተማሪዎች መጫወቻ ሜዳ ምቹነት መጓደል፣ የመምህራን ትምህርት ኮሌጅ ያለበት ደረጃ እንዲሁም የህዝብ ግንኙነት ስራዎች በክፍተት የታዩ መሆናቸውን የቋሚ ኮሚቴው አባላት ለይተው አቅርበዋል።
በትምህርት ዘመኑ ለተከናወኑ ስኬታማ ተግባራት የቋሚ ኮሚቴው ክትትልና ድጋፍ ወሳኝ ሚና ያበረከተ መሆኑን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ገልጸው፤ ከመምህራን ኮሌጅ ግንባታ እና ከተቋማት ስታንዳርድ ማስጠበቅ አንፃር እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን አብራርተዋል።

በሳይንስና ፈጠራ ዘርፍ ተማሪዎች የበለጠ ውጤታማ የሚሆኑበትን ስራዎች ቢሮው በልዩ ትኩረት እያከናወነ እንደሚገኝ የገለፁት የቢሮ ኃላፊው፤ በህዝብ ግንኙነት ዘርፍ በኩል በክፍተት የታዩ አሰራሮችን ለማረም በቀጣይ ሊከናወኑ የሚገቡ ተግባራትንም አንስተዋል።
በታምሩ ደምሴ